የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የኮረና ቫይረስ መከላከል ግብረ ሀይል ስራ ጀመረ

119

መቐለ መጋቢት 08/2012 (ኢዜአ) መቐለ ዩኒቨርስቲ የኮረና ቫይረስ ለመከላከል አስር አባላት ያሉት ቴክኒካል ኮሚቴ በማቋቋም ስራ መጀመሩን አስታወቀ ።
በዩኒቨርስቲው የዓይደር ጤና ኮሌጅ ዲንና የኮሚቴው ሰብሳቢ  ዶክተር አማኑኤል ሀይለ ለኢዜአ እንደገለጹት ቫይረሱ  በተማሪዎች ጤና ላይ ችግር ከማድረሱ በፊት ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል።

 የተቋቋመው ቴክኒካል ኮሚቴ በሁሉም የዩኒቨርስቲው ካምፓሶች  ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በተረጋጋ ሁኔታ ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ  የቫይረሱ መተላለፊያ መንገዶችና የመከላከያ ዘዴዎችን የተመለከተ ተከታታይ ትምህርት መስጠት ጀምሯል።

በዩኒቨርስቲው ስር የሚገኙ ኮሌጆች በቂ ውሀና የእጅ መታጠቢያ ሳሙና እንዲቀርብላቸውም ሞያዊ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በየኮሌጁ ንኡሳን ኮሚቴ ተዋቅረው እንቅስቃሴ መጀመራቸውንም አስረድተዋል።

በጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሚገኙ ባለሞያዎችም ከተማሪው በተጨማሪ የቫይረሱ መከላከያ መንገዶች በበራሪ ጽሁፍና በመገናኛ ብዙሀን ትምህርት በመስጠት ሞያዊ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ይደረጋል ብለዋል።

ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ የሚረዳ 160 ሺህ የአፍና አፍንጫ ጭንብል አምርቶ በክልል ደረጃ ለተቋቋመው ግብረ ሀይል ለማስረከብ ቃል የገባው ደግሞ በመቀሌ  ኩሀ ክፍለ ከተማ የሚገኘው  ማ -ጋርመንት የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ነው።

የፋብሪካው ስራ እስኪያጅ አቶ ፍቅረ ስላሴ አምባው ለኢዜአ እንደገለጹት ፋብሪካው በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ጭምብሉን አምርቶ በነጻ እንደሚያስረክብ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም