በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠው የገጽ ለገጽ ትምህርት በሌሎች የማስተማር ስልቶች እንዲቀየር ተደረገ

74

አዲስ አበባ መጋቢት 08/2012 (ኢዜአ) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከትናንትናው እለት ጀምሮ የገጽ ለገጽ ትምህርቶችን በማቆም በሌሎች የመማር ማስተማር ስልት እንዲቀየር መደረጉን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ።

ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ በሁሉም የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት አስፈላጊ ጥንቃቄና እርምጃ እንዲወስዱ ሚኒስቴሩ መመሪያ ማስተላለፉን አመልክቷል።

የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጉርሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት  የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመግታት መንግስት መጠነ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ ነው።

መንግስት ትናንት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሁለት ሳምንት እንዲዘጉ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ደግሞ ባሉበት እንዲቆዩ ተደርጓል።

በመሆኑም ከዛሬ ጀምሮ በመንግስትም ሆነ በግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የገጽ ለገጽ ትምህርት በሌሎች የመማር ማስተማር ዘዴ እንዲተካ መደረጉን ገልጸዋል።

በየተቋማቱ ተማሪዎች ባሉበት እንዲቆዩ የተደረገው ተማሪዎቹ በንክኪ ሊያጋጥም የሚችልን የበሽታው ስርጭት ለመግታት እንደሆነ ተናግረዋል።

ተማሪዎች ወደ የቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ ማድረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ከግምት ውስጥ እንደገባም አስረድተዋል።

ምክንያቱም ተማሪዎቹ ወደየመጡበት አካባቢ በሚሄዱበት ጊዜ በጉዟቸው ለኮሮናቫይረስ የመጋለጣቸው እድል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል በመስጋት እንደሆነ ገልጸዋል።

ተማሪዎቹ ከዛሬ መጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ባሉበት ሆነው ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚሰጡ መመሪያዎችን እንዲከታተሉና ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መመሪያ ተላልፏል።

ተማሪዎቹ በመምህራኖቻቸው የሚሰጡ ንባቦችን እያካሄዱ ለሁለት ሳምንት የሚቆዩ ሲሆን አስፈላጊ የሆኑ የማጣቀሻ መጽሀፍትና ሌሎች የመማሪያ ቁሳቁሶች በበይነመረብ አማካኝነት እንዲደርሳቸው የሚደረግ መሆኑን አቶ ደቻሳ ተናግረዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም ተቋማቱ ለተማሪዎቹ አስፈላጊ የሆኑ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እንዲሰራጭም ሚኒስቴሩ ትእዛዝ ማስተላለፉን አቶ ደቻሳ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም