ኅብረተሰቡ የበሽታ መከላከያ መንገዶችን ችላ ሳይልና ሳይደናገጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

73

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8/2012 ( ኢዜአ) ኅብረተሰቡ የበሽታ መከላከያ መንገዶችን ችላ ሳይልና ሳይደናገጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥሪ አቀረበ።
ኢንስቲትዩቱ ባወጣው መግለጫ እንዳለው ከመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ጋር ግንኙነት ያላቸውና ተመሳሳይ ምልክት አሳይተዋል በሚል ተጠርጥረው በለይቶ ማቆያ ከነበሩ 113 ተጠርጣሪዎች መካከል 74ቱ በተደረገው የላቦራቶሪ ምርመራ ነጻ መሆናቸው በመረጋገጡ ወደ ሕብረተሰቡ ተቀላቅለዋል።

የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው አምስት ታማሚዎች በለይቶ ማቆያ የህክምና መስጫ ማዕከል የቅርብ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑንና ቀሪዎቹ 34 ተጠርጣሪዎች ደግሞ በለይቶ ማቆያ ሆነው የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

በቫይረሱ መያዛቸውን ማረጋገጥ ከተቻለው 5 ግለሰቦች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው 992 ሰዎች ባሉበት ቦታ ለ14 ቀናት የጤና ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን ሌሎች 1 ሺህ 285 ሰዎች ደግሞ ለ14 ቀን የጤና ክትትል ተደርጎላቸው ጤንነታቸው በመረጋገጡ ክትትላቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል።

በሁሉም ወደ ሀገር መግቢያ ጣቢያዎች እየተደረገ ያለው አገር አቀፍ ምርመራ ተጠናክሮ መቀጠሉን በመግለጽ፤ እስካሁን በሙቀት መለያ ያለፉት ቁጥር በሽታውን ሪፖርት ካደረጉ አገራት 8 ሺህ 985 መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።

ኢንስቲትዩቱ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታትና ለመቆጣጠር በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው ህብረተሰቡ ማንኛውንም በሽታ ለመከላከል ሲጠቀምባቸው የነበረውን ባህላዊ የመከላከያ ዘዴዎችን ችላ ሳይልና ሳይደናገጥ እንዲጠቀም መክሯል።

በዚህም ሳል ወይም ትኩሳት ካለው ግለሰብ ቢያንስ ሁለት የአዋቂ እርምጃ ርቀት ያህል መራቅ፣ እጅን በንጹህ ውሃና ሳሙና አዘውትሮ መታጠብ፣ ወይም እጅን በአግባቡ ሳይታጠቡ አይንና አፍንጫን አለመንካት፣ ከሰዎች ጋር አለመጨባበጥን ተግባራዊ እንዲያደርግም ጠይቋል።

የህመም ስሜት ከተሰማ ሰዎች በሚበዙባቸው ስፍራዎች አለመገኘት፣ ሲያነጥሱና ሲስሉ አፍንጫን በሶፍት ወይም ክርንን አጥፎ መጠቀም፤ የተጠቀሙበትን ሶፍትና ተመሳሳይ ነገሮች ክዳን ባለው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ማስወገድ እንደሚገባ ገልጿል።

በተጨማሪም በስራ ቦታ፣ በትራንስፖርትና መኖሪያ ወይም የመኝታ ክፍል መስኮት በመክፈት በቂ አየር እንዲኖር ማድረግም እንደሚጠበቅ አስታውቋል።

መረጃዎችን ከአስተማማኝ ምንጮች ብቻ በመቀበል፣ የተሳሳቱ መረጃዎች የሚያስከትሉትን መደናገርና ፍርሀት መከላከል እንደሚገባም ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።

በጉዳዩ ላይ መረጃ ለመለዋወጥ በ8335 የስልክ መስመር ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 ወይም በኢሜል አድራሻ ephieoc@gmail.com መጠቀም ይቻላል ተብሏል።

ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት መጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 174 ሺህ 881 የደረሰ ሲሆን 77 ሺህ 781 ሰዎች ጤንነታቸው ተመልሷል።

በዓለም ላይ 158 አገራት የኮሮና ቫይረስ እንደተከሰተባቸው ይፋ ያደረጉ ሲሆን ቫይረሱ እስካሁን የ6 ሺህ 526 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም