በበጎ ፈቃደኞች ላይ አሜሪካ የኮሮናቫይረስ ክትባት ሞከረች

76

መጋቢት 8/2012 አሜሪካ ኮቪድ-19ን መከላከል የሚያስችል ክትባት ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ላይ ሞከረች።

አራት በኮሮናቫይረስ የተያዙ አሜሪካውያን ሲያትል በሚገኝ የምርምር ማዕከል ክትባቱን ወስደዋል።

ክትባቱ ኮቪድ-19 ከሚያሲዘው ቫይረስ ጎጂ ያልሆነ የጄኔቲክ ኮድ ኮፒ ተደርጎ የተወሰደ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ይገልጻሉ።

ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ክትባቱ መስራት አለመስራቱን ለማወቅ በርካታ ወራት ይጠይቃል።

የ43 ዓመቷ የመጀመሪያዋ በጎ ፈቃደኛ ጄኔፈር ሀለር፣ የሁለት ልጆች እናት ስትሆን በትናንትናው ዕለት ክትባቱን ስትወስድ "አንድ ነገር ለማድረግ በመቻሌ ለኔ ይህ ትልቅ እድል ነው " ስትል ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ተናግራለች።

በዓለማችን ላይ የሚገኙ የተለያዩ አገራት ተመራማሪዎች የቫይረሱን መከላከያ ክትባት ለማግኘት ደፋ ቀና እያሉ ነው።

እናም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ላይ የተደረገው ሙከራ ከዚህ በፊት ክትባቱ የመከላከል አቅምን ያዳብር እንደሆን በእንስሳት ላይ የሚደረገውን ሙከራ ወደ ጎን ያለ ነው ተብሏል።

ነገር ግን ከዚህ ምርምር ጀርባ ያለው የባዮቴክኖሎጂ ኩባንያ፣ ሞደርና ቴራፒዩቲክስ፣ ክትባቱ አስፈላጊውን የሙከራና የፍተሻ ሂደቶችን ያለፈ ነው ሲል ማረጋገጫ ሰጥቷል።

ዶ/ር ጆን ትሬጎኒንግ በኢምፒሪያል ኮሌጅ ለንደን የተላላፊ በሽታዎች ተመራማሪ ሲሆኑ " ክትባቱ ቀድሞ የነበረን ቴክኖሎጂ ይጠቀማል" ብለዋል።

አክለውም " ክትባቱ የተሰራው በከፍተኛ ሁኔታ ደረጃቸውን በጠበቁ፣ ሰው ላይ ለመጠቀም ደህንነታቸው በተረጋገጠ ነው። ሙከራው ላይ የሚሳተፉም የቅርብ ክትትል ይደረግላቸዋል" ሲሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በመቀጠልም "አዎ በርግጥ ይህ ሙከራ ፈጥኗል። ነገር ግን እሽቅድምድም የያዝነው ተመራማሪዎች እርስ በርሳችን ሳይሆን ከቫይረሱ ጋር ነው። የሚሰራውም ለሰው ልጅ ትርፍ ተብሎ ነው" ብለዋል።

የኮቪድ 19 ክትባት ለመውሰድ ፈቃደኛ የሆኑት ሕሙማን ላይ የተለያየ መጠን ያለው ክትባት ነው የተሰጣቸው።

ግለሰቦቹ በ28 ቀናት ልዩነት ክንዳቸው ላይ ሁለት ክትባት የሚወጉ ይሆናል።

ይህ ሙከራ እንኳ የሚሳካ ቢሆን ለአጠቃላይ ማህበረሰቡ ዝግጁ ለማድረግ 18 ወራት እንደሚፈጅ ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም