በሐረር ከተማ የኮሮና ቫይረስ ምርመራና ህክምና መስጫ ማዕከል ተቋቋመ

65

ሐረር/ ሰመራ፣ መጋቢት 8/2012 (ኢዜአ) በምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ምርመራና ህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል በሐረር ከተማ ተቋቋመ።

ከጂቡቲ ወደ ሀገር በሚገባ የየብስ ትራንስፖርት  ኮሪደር በኩልም ቫይረሱን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን  የአፋር ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።

በሐረር ከተማ የተቋቋመው ማዕከል በህይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ ነው።

የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ኢብሳ ሙሳ  እንደገለጹት በማዕከሉ በሶስት ፈረቃ 24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡ ከስፔሻላይዝድ ዶክተር እስከ ጤና ረዳት የጤና ባለሙያዎች ተመድበዋል።

ከሐረሪ ክልል መንግስትና ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበርም ለህክምናው የሚረዱ በቂ የቁሳቁስና መድኃኒት አቅርቦት ለማዕከሉ መሟላቱን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅትም ሙሉ ግብዓት የተሟላላቸው  20 አልጋዎችን በመያዝ ማዕከሉ ስራ መጀመሩን አመልክተው እንደ አስፈላጊነቱ የታካሚው ቁጥር ከጨመረ በቂ ቦታ፣ባለሙያና ግብዓት መመቻቸቱን ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ የድንገተኛና ጽኑ ህሙማን ስፔሻሊስት ዶክተር ናታን ሙሉ ብርሃን በበኩላቸው ማዕከሉ በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩ ሰዎች ምርመራ የሚያከናውኑበት እንዲሁም ቫይረሱ የሚገኝባቸው ህሙማንን ህክምና መስጠት የሚያስችል ክፍል ተለይቶ መዘጋጀቱን አረጋግጠዋል።

ባለሙያውም ለህክምና አገልግሎቱ በቂ ስልጠና ወስደው  ለስራው ዝግጁ ሆነዋል።

የክልሉ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገሪቱ ከመግባቱ አስቀድሞ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱን የገለጹት ደግሞ በሐረሪ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ዮኒስ ናቸው።

በተለይም የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማስፋት አንጻር ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው በተለይ በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡን የማንቃት ስራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በሐረሪ ክልል እስካሁን ድረስ በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠረም ሆነ የተያዘ  ግለሰብ አለመኖሩንም አቶ ኤሊያስ አስታውቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከጅቡቲ ወደ ሀገር በሚገባ የየብስ ትራንስፖርት  ኮሪደር በኩልም ቫይረሱን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን  የአፋር ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገልጿል።

በሶስት ሳምንታት ውስጥ ከጅቡቲ ጋር በሚያገናኘው የጋላፊ ኬላ በኩል ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ  ከ37 ሺ በላይ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ  እንደተደረገለዓቸው የኢንስቲትዩቱ አስተባባሪ አቶ አብዱ አሊ ተናግረዋል።

በክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር የሚመራ አብይ ኮሜቴ ተዋቅሮ  ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በሰመራ ሱልጣን አሊሚራህ ሃንፈሬ አውሮፕላን ማረፊያም የሚገቡና የሚወጡ ተጓዧች ላይም ምርመራ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በክልሉ ከጂቡቲና ኤርትራ ጋር በሚያዋስኑ  ወረዳዎች የቁጥጥርና  ለህብረተሰቡም ስለ ቫይረሱ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተካሄደ ነው።

በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች በጊዜያዊነት የሚቆዩበት ማዕከል በጋላፊ ኬላ መዘጋጀቱን ያመለከቱት አስተባባሪው በዱብቲና በመሃመድ አክሌ ሆስፒታል ህክምና ሊሰጥ የሚያስችል የባለሙያዎች ስልጠና የግብአት ማሟላት ስራ ተከናውኗል።

እስካሁንም በአካባቢው በቫይረሱ የተጠረጠረም ሆነ የተያዘ እንደሌለም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም