የቋንቋ ፖሊሲው የፌዴራል ስርዓቱን የሚያጠናክርና ቀደም ሲል ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን የሚመልስ መሆኑ ተገለፀ

144

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 07/2012 (ኢዜአ) የቋንቋ ፖሊሲው የፌዴራል ስርዓቱን የበለጠ የሚያጠናክር እና በብሄር ብሄረሰቦች በተደጋጋሚ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን በአደረጃጀት የሚመልስ መሆኑ ተጠቆመ።

በቋንቋ ፖሊሲ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዛሬ ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩ ላይ በቋንቋ ፖሊሲ ይዘትና አተገባበሩ ላይ በምሁራን የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የመነሻ ጽሑፉን ያቀረቡት፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዶክተር ታዬ አበራ እና ዶክተር ሞገስ እዮብ፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ደግሞ አቶ አውላቸው ሹምነካ ናቸው።

የቋንቋ ፖሊሲው በውስጡ የያዛቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ያነሱት የጽሁፍ አቅራቢዎቹ ለአብነትም የስራ ቋንቋ፣ የመገናኛ ብዙሃንና የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ቋንቋ አጠቃቀም፣ ቋንቋ እና ትምህርት፣ የአደባባይ ቋንቋ አጠቃቀም እንዲሁም ትርጉምና አስተርጓሚነት የሚሉ ነጥቦችን አንስተዋል።

ሁሉም ቋንቋዎች በህገ-መንግስቱ እኩል መብት ተሰጥቷቸው ያደጉ ቢሆኑም ለቋንቋዎች እድገት ስርዓት ባለመበጀቱ በሚፈለገው ልክ ውጤት አለመመዝገቡን ተናግረዋል።

ለአብነትም በኢትዮጵያ በርካታ ቋንቋዎች ቢኖሩም ብዝሃ ልሳን ያለው ማህበረሰብ መፍጠር ያልተቻለበት ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረው ፤ ፖሊሲው ይህንን እና መሰል ችግሮችን ይፈታል ብለዋል።

ምሁራኑ ፖሊሲውን ተቋማዊ ለማድረግ ብሄራዊ የቋንቋ ጉዳዮች ምክር ቤት ፣ የቋንቋዎች ጥናት ማዕከሎች፣ እና የትርጉም ተቋም መመስረት አስፈላጊ መሆኑንም አስምረውበታል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው ኢትዮጵያ የብዝሃ ቋንቋና ባህል ባለቤት አገር መሆኗን ተናግረዋል።

ይህንን ቋንቋና ባህል ለማሳደግ የህግ ማዕቀፍና ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሰራበት መቆየቱን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 በላይ ቋንቋ ስለ መኖሩ የተናገሩት ሚኒስትሯ ፤ ይሄንን ሀብት ለማልማት የፖሊሲ ማዕቀፍ አስፈላጊ መሆኑንም አብራርተዋል።

በመድረኩ  ተሳታፊ የነበሩ ባለድርሻ አካላትም ፖሊሲው የፌዴራል ስርዓቱን የበለጠ ያ0ናክራል ፤ በብሄር ብሄረሰቦች ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን በአደረጃጀት ይመልሳል ብለዋል።

በአገሪቱ የሚነገሩ ቋንቋዎች ሁሉ ዜጎች "የራሴ ነው" የሚል እምነት እንዲያሳድሩም ያግዛል ተብሏል።

አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ እና ውጤት ሊያስገኝ የሚችል ስለመሆኑም ተናግረዋል።

አማርኛ ቋንቋ በአገር ወስጥ ያለው የተናጋሪዎች ብዛትና የተደራሽነት ስፋት እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ የፓለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ተግባቦትን ለማሳለጥ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋዎችን መጠቀም አንዱ መንገድ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቋንቋ ፖሊሲው አሁን ያለውን የአማርኛ ቋንቋን ጨምሮ አምስት ቋንቋዎች በስራ ቋንቋነት እንዲያገለግሉ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን አፈጻጸሙም በህገ-መንግስቱ ማሻሻያ የሚታይ እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም