የመድኃኒት አስመጪዎች፣ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ሙያዊ ስነ-ምግባራቸውን ጠብቀው ሕብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ተጠየቀ

89

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 07/2012 (ኢዜአ) የመድኃኒት አስመጪዎች፣ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ሙያዊ ስነ-ምግባራቸውን ጠብቀው ሕብረተሰቡን እንዲያገለግሉ የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አሳሰበ።

ባለሥልጣኑ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ በሚገኙ መድኃኒት ቤቶች ድንገተኛ ቁጥጥር አድርጓል ፤ ከመድኃኒት አስመጪዎችና አከፋፋዩች ጋርም ውይይት አድርጓል።


የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ በመድሃኒት ቤቶች ያለውን የኬሚካልና ሌሎች ቁሳቁሶች አቅርቦት በተመለከተ ድንገተኛ ፍተሻ አድርጓል።

ባለስልጣኑ ባደረገው ድንገተኛ ቁጥጥርም በተጋነነ ዋጋ ሲሸጡ ያገኛቸው መድሃኒት ቤቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።

በቀጣይም ተመሳሳይ ተግባር የሚፈፅሙ የመድኃኒት መደብሮች ሲያጋጥሙ ህብረተሰቡ በ8482 ነፃ የስልክ መስመር እንዲያሳውቅ ባለሥልጣኑ መልእክቱን አስተላልፏል።

የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አበራ ደነቀ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተገለፀ ወዲህ አንዳንድ ህገ ወጦች በተለይ በኬሚካልና የአፍ መሸፈኛ ማስክ ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ መሸጣቸው ተደርሶበታል።

ይህንን ባደረጉ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውሰው፤ ቀጣይም ይሄው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የዛሬው ድንገተኛ ቁጥጥርም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ያልተገባና የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ከሙያዊ ስነ-ምግባር አንፃር ተገቢ ያልሆነ ፤ አስመጪውን፣ አከፋፋዩንና ቸርቻሪውን የሚያስጠይቅ መሆኑንም አሳስበዋል።

በመሆኑም ባለስልጣኑ ዛሬ በአዲስ አበባ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ በጎሮና በመገናኛ አካባቢ በተጋነነ ዋጋ ቁሳቁሶቹን ሲሸጡ የተገኙ ሁለት መድሃኒት ቤቶች ላይ እርምጃ ወስዷል።

ከአዲስ አበባ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም ደንብ ማስከበርና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የቁጥጥር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት ሕብረተሰቡ መረጋጋት ይጠበቅበታል ያሉት አቶ አበራ ፤ በየመንገዱ የሚሸጡና ንጽህናቸውን ያልጠበቁ የፊት መሸፈኛ  ማስኮችን ከመግዛትና ከመጠቀም እንዲቆጠብ አሳስበዋል።

በዛሬው እለት ባለስልጣኑ ከመድኃኒት አስመጪዎችና አከፋፋዬች ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን ሙያዊ ስነ-ምግባራቸውን አክብረው ሕብረተሰቡን እንዲያገለግሉም አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም