የራያ ዩኒቨርስቲ የግጭት መንስኤዎችን ለይቶ ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገለፀ

62

መቐለ፣ መጋቢት 07/2012 ዓ.ም (ኢዜአ) የራያ ዩኒቨርስቲ ተጎራባች በሆኑ ህዝቦች መካከል የግጭት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን በመለየት ባህላዊና ሳይንሳዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገለፀ ። 

ዩኒቨርስቲው በተጎራባች ክልሎች ላይ ዘላቂ ሰላም ለማስቀጠል አገር በቀልና ሳይንሳዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን አስመልክቶ ለአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች የሁለት ቀናት ስልጠና ሰጥቷል።

የራያ ዪኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዚደንትና የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ኃላፊ ዶክተር ክብሮም ካህሱ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የተጎራባች ህዝቦች ሰላማዊ ግንኝነት ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል በትኩረት እየሰራ ነው።

ዩኒቨርስቲው ለህዝቦቹ ግንኝነት መሻከርና ለግጭት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን በጥናትና ምርምር የመለየት ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል ።

ስልጠናው ግጭቶችን ለመከላከል በሚያስችሉ የአገር በቀል እውቀቶችና ሳይንሳዊ የግጭት መከላከልና አፈታት ዘዴዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን አስረድተዋል ።

ዩኒቨርሲቲው ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት ማህበረሰቡ አስቀድሞ እንዲከላከላቸው  የማንቃት ስራ በቀጣይነት እንደሚሰራም ዶክተር ክብሮም ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ከነበሩ ነዋሪዎች መካከል የራያ አላማጣ ወረዳ የእስልምና ጉዳዮች ኃላፊ ሼኽ ያሲን ሁሴን በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ከአከባቢው ማህበረሰብ አልፎ ለአገር ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ጠቃሚ ግብአት እንዳገኙበት ተናግረዋል።

በተለይም የራያ አላማጣ ወረዳ ህዝብ ወንድም ከሆነው የአማራ ክልል ህዝብ ጋር የቆየው ግንኙነት እንዲሻክር መንስኤ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ በአጭሩ መቅጨትና ወደ ሰላም ለመመለስ የሚጠቅም ትምህርት ያገኙበት ስልጠና እንደነበር ገልፀዋል ።

የትግራይና የአማራ ህዝቦች ታሪካቸውን መሰረት ያደረገ ግንኙነት እንዲኖርና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ሼኽ ያስን ተናግረዋል።

"አገሪቱ የብጥብጥና የሁከት መናኽሪያ እንድትሆን ወጣቶች እንደ መሳሪያ ለመጠቀም የሚጥሩ አካላት መታገል እንዳለብን ተረድቻለሁ"ያለችው ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊና የአላማጣ ከተማ ነዋሪ  ወጣት ፋና ብርሃኑ ነች።

በብሄር፣ በሃይማኖትና በአካባቢ  እየከፋፈሉ  ህዝብ ከህዝብ ጋር የሚያጣሉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለማድረግ እንዲህ አይነት የውይይት መድረክ ማዘጋጀት አስፈላጊ እንደሆነም ወጣቷ  ተናግራለች።

በውይይት መድረኩ ላይ ከትግራይ ደቡባዊ ዞን  የተውጣጡ ከ400 በላይ የሚሆኑ የሃይማኖት አባቶች ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም