ከዛሬ ጀምሮ ለአንበሳና ለሸገር አውቶቡስ ተሳፋሪዎች የእጅ ንፅህና መጠበቂያ ኬሚካል ይቀርባል - ኢንጂነር ታከለ ኡማ

84

አዲስ አበባ መጋቢት 07/2012 (ኢዜአ) የአንበሳና ሸገር አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅቶች ለተሳፋሪዎች የእጅን ፅህና መጠበቂያ ኬሚካል እንደሚያቀርቡ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አስታወቁ።

የኮሮና ቫይረስን መከላከል እንዲቻል ለሁለት ሳምንት ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ ስፖርታዊ ውድድሮችና ህዝባዊ ስብሰባዎች እንዳይደረጉ መወሰኑን ኢኒጂነር ታከለ አውስተዋል።

ይህን ተከትሎም ድርጅቶቹ የተሳፋሪዎችን ንጽህና ለመጠበቅ የእጅ ኬሚካል እንደሚያቀርቡ መግለጻቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአውቶቡሶቹ አሽከርካሪዎች የእጅ ጓንት የሚጠቀሙ ሲሆን ተሳፋሪዎችም ወደ አውቶቡሶች ሲገቡ ድርጅቶቹ የሚያቀርቡትን የእጅ ኬሚካል እጃቸው ላይ በማድረግ እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል በሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረ ኃይል በመዲናዋ ጠንካራ ቁጥጥር እያካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።

ለህዝብ አገልግሎት ሰጪዎችና በጎ ፈቃደኞችም አቅም የሌላቸውን እንዲሁም ውሃና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ማግኘት የማይችሉትን መደገፍ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ የከተማውን ሕዝብ ጤና ለመጠበቅ ጠንክሮ እንደሚሰራ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም