በቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ወላይታ ድቻ ሙገር ሲሚንቶን አሸነፈ

57

አዲስ አበባ መጋቢት 07/2012 (ኢዜአ) በሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ወላይታ ድቻ ሙገር ሲሚንቶን አሸንፏል።

መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ መሪነቱን አጠናክሯል።

የፕሪሚየር ሊጉ 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትናንትና እና ከትናንት በስቲያ በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በሳምንቱ በፕሪሚየር ሊጉ ይጠበቅ የነበረው የአምናው የሊጉ አሸናፊ ወላይታ ድቻ እና ሙገር ሲሚንቶ ጨዋታ ባለሜዳው ወላይታ ድቻ በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 1 አሸንፏል።

ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ ነጥቡን ወደ 25 ከፍ በማድረግ በነበረበት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀጥል ሙገር ሲሚንቶ በ22 ነጥብ በነበረበት ሶስተኛ ደረጃ ረግቷል።

የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተካሄዱት ሰባት ውድድሮች አሸናፊ የሆኑት ወላይታ ድቻና ሙገር ሲሚንቶ ብቻ ናቸው።

ወላይታ ድቻ አራት ጊዜ ሙገር ሲሚንቶ ሶስት ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ሆነዋል።

ትናንት ሮቤ ላይ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ መከላከያን በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ3 ለ 1 ረትቷል።

ውጤቱንም ተከትሎ መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ነጥቡን ወደ 26 ከፍ በማድረግ መሪነቱን አጠናክሯል።

ትናንት ባህርዳር ላይ በተደረገ ጨዋታ አዲስ አበባ ፖሊስ ጣና ባህርዳርን በሶስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 0 አሸንፏል።

ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ የ10ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን 3 ለ 1 ረትቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም