በመዲናዋ ያለው የመድሃኒት ስርጭትና አቅርቦት ችግር እየተሻሻለ ነው ተባለ

133
አዲስ አበባ ሰኔ 22/2010 በአዲስ አበባ ያለውን የመድሃኒት ስርጭትና አቅርቦት ስርዓት ለማስያዝ በተወሰደው የተቀናጀ እርምጃ በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ መሰረታዊ የሆኑ መድሃኒቶች አቅርቦት እየተሻሻለ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በአዲስ አበባ  የመሰረታዊ መድሃኒቶች አቅርቦትና ስርጭት ችግር እየተስተዋለ መሆኑ ይነገራል። ሆኖም ይህ ችግር በአሁኑ ወቅት እየተሻሻለ መምጣቱን ነው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ዳይሬክተር አቶ ረጋሳ ባይሳ ለኢዜአ የተናገሩት። በመዲናዋ የመድሃኒት ስርጭቱ ችግሩን ማሻሻል የተቻለው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያግዝ ስርዓት በመዘርጋቱ መሆኑን አቶ ረጋሳ ገልፀዋል። በዚህም መሰረት በተለይ በሆስፒታሎችና በጤና ተቋማት አካባቢ ባለፉት ቅርብ ጊዜያት በአማካኝ 45 በመቶ የነበረው የመሰረታዊ መድሃኒቶች አቅርቦትና ስርጭት በአሁኑ ወቅት ወደ 85 በመቶ ማደጉን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። በአዲስ አበባና በክልሎች የመድሃኒት አቅርቦት እጥረት ችግር ለመቀነስና የመድሃኒት አገልግሎት አሰጣጡን ስርዓት ማሻሻል እንዲቻል የተለያዩ ቡድኖች ተዋቅረው ወደሥራ መሰማራታቸውንም ገልፀዋል። የጤና ተቋማት ኃላፊዎች፣ የመድሃኒት አቅርቦትና ፈንድ፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቡድኖቹ ከተካተቱት አካላት መካከል መሆናቸውንም አቶ ረጋሳ ጠቅሰዋል። አቶ ረጋሳ እንዳሉት የጤና ተቋማት የመድሃኒት ቆጠራ እንዲያካሂዱ በማድረግም በአንዳንድ የጤና ተቋማት የሌሉ መድሃኒቶች በሌሎች የጤና ተቋማት ያለአግባብ ተከማችተው መገኘታቸውን ማረጋገጥ ተችሏል። በዚህም እጥረት ይስተዋልባቸው በነበሩት የጤና ተቋማት ያለ ተጨማሪ የመድሃኒት አቅርቦት የመሰረታዊ መድሃኒቶች አቅርቦት ችግሩን ማቃለል እንደተቻለ ነው ያብራሩት። ይህም የአሰራር ስርዓት የመድሃኒት ብክነት ችግርን ለመቀነስ፣ በጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ግልጽነት ለመፍጠርና ብልሹ አሰራርን ለመቀነስ ማስቻሉን ተናግረዋል። የጤና ተቋማት በሚሰጧቸው የህክምና አገልግሎቶች መሰረት ወሳኝ፣ መካከለኛና ብዙም ተፈላጊ ያልሆኑ መድሃኒቶች እንዲለዩ ተደርጓል። መድሃኒቶች በህብረተሰቡ ዘንድ ባላቸው ተፈላጊነት መሰረት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል የሚባሉትን በመለየት የመድሃኒቶች ግዢ እንዲፈጸም የሚያደርግ አሰራር በመዘርጋት አቅርቦቱን ለማሻሻል የሚያስችል ጥረት ተጀምሯል። አሰራሩ የመድሃኒት አቅርቦትና ግዢ በተጨባጭ መረጃ መሰረት እንዲካሄድና እንዲፋጠን ከማገዝ ባሻገር ተገልጋዮችን ከእንግልትና ከአላስፈላጊ ወጪ እየታደጋቸው መሆኑንም ነው አቶ ረጋሳ የገለፁት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም