የኮሮናቫይረስ መከሰቱን ከተነገረ በኋላ በሸቀጦች ላይ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ ነው

81

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ አገር ውስጥ መግባቱ ከተገለጸ በኋላ በተለያዩ ሸቀጦችና የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ የከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ኢዜአ በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ እንደታዘበው በአንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች ምርቶችን ለመግዛት ረጃጅም ሰልፎችን ይዘው ሲጠባበቁ ተመልክቷል።

በተለይም የአፍ መሸፈኛ ወይም ማስክ፣ የንጽህና መጠበቂያ (ሳኒታይዘር)፣ ሎሚ፣ ነጭ ሽንኩርትና ሌሎች ምርቶችም በተጋነነ ዋጋ ሲሸጥ ተስተውሏል።

በተለይ ሎሚና ነጭ ሽንኩርት ፈላጊዎች ከወትሮው በሶስት እጥፍ ዋጋ መግዛታቸውን ነግረውናል።

በተለይ የአፍ መሸፈኛ እና ሳኒታይዘር በአብዛኛው የአዲስ አበባ ማድሃኒት ቤቶች እጥረት እንዳለ የፋርማሲ ባለቤቶችና ሲገዙ ያገኘናቸው ሸማቾች ተናግረዋል።

በ70 ሳንቲም ይሸጥ የነበረው የአፍ መሸፈኛ ማስክ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ከ100 እስከ 150 ብር በህገ ወጦች ሲሸጥ ታይቷል።

በፋርማሲዎች አካባቢ መድሃኒት ለመግዛት የሚመጡ አዛውንቶችና ነፍሰጡሮች ማክስና ሳኒታይዘር ለመግዛት በሚደረገው ግፊያ ሲንገላቱም ለመመልከት ተችሏል።

የህክምና ባለሙያዎች እንደሚመክሩት ከሆነ የአፍ መሸፈኛ ማስክ ማድርግ ያለባቸው በህክምና ስራ ላይ ያሉ ሃኪሞች፣ ታማሚዎችና በዚሁ አካባቢ የተገኙ ሰዎች ናቸው።

አንዳንድ ግለሰቦችም የተለያዩ ሸቀጦችን በመግዛት በቤታቸው እያከማቹ መሆኑን መመልከታቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።

መንግስት ሸቀጦችን በመደበቅ ዋጋ በመጨመር ህዝብ የሚያማርሩ ግለሰቦችና ነጋዴዎች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወሰድ ምስላቸው እንዳይቀረጽ የፈለጉ አስተያየት ሰጪ ተናግረዋል።

በትላንትናው እለት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ተገኝቷል በሚል ከወጣው መረጃ በኋላ በአዲስ አበባ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን የሚቆጣጠር ግብረ-ሀይል መቋቋሙን የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤተ መግለጹ ይታወቃል።

በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የሚመራው ግብረ-ሀይሉ ባልተገባ መልኩ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑንም አስታውቋል።

ህብረተሰቡ ካልተገባ የዋጋ ጭማሪ ራሱን እንዲጠብቅና በዚህ አይነት መልኩ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ሲመለከትም በ011 155 33 43 የስልክ መስመር ጥቆማ እንዳያደርስ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም