"ፓርኩ አገራዊ ማንነትን አጉልቶ የሚያሳይ ነው" ... የኢዜአ ሰራተኞች

78

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2012( ኢዜአ)የአንድነት ፓርክ አገራዊ ማንነትን አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሰራተኞች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሰራተኞች በታላቁ ቤተመንግስት ቅጥር ግቢ የሚገኘውን የአንድነት ፓርክ በዛሬው እለት ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸው ልዩ ልዩ የታሪክ፣ የተፈጥሮ እና የባህል መስህቦችን ጨምሮ የታነፁ ታሪካዊ ህንፃዎችን፣ የዱር እንስሳት መስህቦችን የሚያስተዋውቁ  እልፍኞችን ተመልክተዋል።

በተጨማሪም የአገር በቀል እጽዋት ስፍራ፣ የአረንጓዴ ቦታዎችን ጨምሮ ሌሎች የፓርኩን የጉብኝት መዳረሻዎች  ለመመልከት ችለዋል።

በጉብኝቱ 175 ሜትር ርዝመት ባለው ዋሻ ውስጥ ሆነው እየተዘዋወሩ በባሌ እና በደዴሳ አካባቢ የሚገኘውን ባለ ጥቁር ጎፈር አንበሳ የተመለከቱት ሰራተኞቹ ባዩት ነገር መደመማቸውን ገልፀዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት ፓርኩ ኢትዮጵያዊ ማንነትን አጉልቶ የሚያሳይ ልዩና የሚደነቅ ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል።

ፓርኩ ውስጥ መግባት ከመዝናናት ባለፈ አገርን ማወቅ፣ ተፈጥሮን ማየት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን መጎብኘት መሆኑንም ይናገራሉ።

በአንድነት ፓርክ ከተካተቱት የክልሎች እልፍኞች የብሔር ብሔረሰቦች ባህል የሚንፀባረቅበት ስፍራ ከመሆኑ ባሻገር ስፍራው በብሔር ብሔረሰቦች ቤት፣ ባህል፣ ምጣኔ ኃብትና የሕዝቦችን አኗኗር መሰረት በማድረግ ላይ መሆኑ የኢትዮጵያዊያን አንድነትን እና አገራዊ ማንነት አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ፓርኩ የተሰራበት ስፍራ አቧራው ተራግፎ፣ ቆሻሻው ተወግዶ ያማረ እና ለአይን ማራኪ ማድረግ ከተቻለ አጠቃላይ ኢትዮጵያን ለመቀየር  ከተሰራ ምንም ማድረግ እንደሚቻል አመላካች ነው ብለዋል።


የአንድነት ፓርክ የሚገኝበት ታላቁ ቤተ መንግስት የተቆረቆረው በ1878 ዓ.ም ሲሆን የመሰረቱትም በወቅቱ የሸዋ ንጉስ የነበሩት ዳግማዊ ዐጼ ምኒሊክ እና ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ቡጥል ናቸው።

በቤተ መንግስቱ ከ1878 ዓ.ም ጀምሮ 7 መሪዎች ኢትዮጵያን አስተዳድረውበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የፓርክ ስፍራ ተዘጋጅቶለት ለጎብኝዎች ክፍት ሆኗል፤ በውስጡም በርካታ ማራኪ መስህቦችን ይዞ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም