የፖለቲካ ልዩነት ቢኖርም በህዳሴው ግድብ ላይ ግን የጋራ አቋም ያስፈልጋል- ኦባንግ ሜቶ

178

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2012 (ኢዜአ) "የፖለቲካ ልዩነቶች ቢኖሩም በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ግን የጋራ አቋም በመያዝ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ለዓለም ማሳየት አለብን" ሲሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ ተናገሩ። 

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የተለያዩ አገራት የሚያሳድሩትን ጫና በመቋቋም፣ የአገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ መንግስት የያዘውን አቋም አድንቀዋል።

አገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት ባስመዘገበችው ታሪክ  የውጭ ችግር ሲያጋጥማት በጋራ መመከት የተለመደ መሆኑን ያነሱት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ይህንንም ታሪክ የአሁኑ ትውልድ ለአገሩ እድገትና ልማት ሊደግመው ይገባል ብለዋል።

በአገር ውስጥ በፖለቲካ ተሳትፎ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችም ይሁን አባላት ምንም አይነት የፖለቲካ ልዩነት ቢኖርባቸው በአባይ ጉዳይ ግን በጋራ መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ዛሬም ኢትዮጵያ የራሷን ሃብት ለመጠቀም የምታደርገውን ጥረት የሚያጨናግፉ አካላትን በጋራ ለመመከት፣ በፖለቲካውም ሆነ በሌላ ልዩነት ያላቸው  አካላት በጋራ ሆነው መንቀሳቀስ አለባቸው ብለዋል።

የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ህዝብ ህልውና በመሆኑ "የሰው ሳይነኩና የራስን ሳያስነኩ" በመኖር ከአባቶች የወረስነውን አኩሪ ታሪክ ማስቀጠል ይገባልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በህዝቦቿ ጥረትና ድጋፍ እየገነባች ያለችው የህዳሴ ግድብ የህልውናዋ መሰረትና የመሰረታዊ ፍላጎቷ ማሟያ በመሆኑ ማንም ሊያስቆማት አይችልም ብለዋል።

በመሆኑም በአገራዊ ጥቅማችን ላይ የጋራ አቋም በመያዝ አብረን ልንቆም ግድ ይላል ብለዋል።

መንግስትም  ማንንም በማይጎዳ መልኩ ኢትዮጵያ የራሷን ሃብት ለመጠቀም የጀመረችውን ጥረት ዳር ለማድርስ መስራት አለበት ብለዋል።

የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በሰላማዊ መንገድ እንዲቀጥል በማድረግ በተለይ ምሁራንና ታዋቂ ግለቦች በዘርፉ እገዛ ሊያደርጉ ይገባልም ነው ያሉት።

‘’መንግስት ይመጣል መንግስት ይሄዳል፤ ህዝብ ግን ይቀጥላል’’ ያሉት ኦባንግ "ለጋራ ቤታችን ኢትዮጵያ" የሁላችንንም ትብብር ይጠይቃል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሚድርስባትን የውጭ ጫና፣ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ከሌሎች አቻ የውጭና የአገር ውስጥ ተቋማት ጋር የድርሻቸውን ለማበርከትም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

  የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ የህዝቡ ሁለንተናዊ ድጋፍና እገዛ በቀጠል ይኖርበታልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም