በምርጥ ዘር ብዜት በመሳተፋቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን የምዕራብ ኦሮሚያ አርሶ አደሮች ገለጹ

108

ነቀምቴ መጋቢት4/2012 (ኢዜአ )የምርጥ ዘር ብዜቱ ላይ መሳተፋቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የምዕራብ ኦሮሚያ አርሶ አደሮች ገለጹ።...

የክልሉ ምርጥ ዘር ኢንተር ፕራይዝ የምአራብ ቅርንጫፍ ለ2012/13 የምርት ዘመን ከ60ሺ ኩንታል የሚበልጥ ከፍተኛ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ የተለያዩ የበቆሎ ምርት ዘሮችን ማዘጋጀቱን አስታወቋል።

በቡኑ በደሌ ዞን የጨዋቃ ወረዳ የጀገን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሻፊ አለሙ እንደተናገሩት ቀደም ሲል በ2011/12 የምርት ዘመን በምርጥ ዘር ብዜት መሳተፍ በመቻላቸው የተሻለ ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው የሚችል ምርት ማግኘት ችለዋል።

በአንድ ሄክታር መሬታቸው ላይም 37 ኩንታል ምርጥ ዘር አባዝተው በ35ሺህ 150 ብር ለመሸጥ በመቻላቸው ጥሩ ገቢ ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።

የመቀርሳ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ፀባይ ጥላሁን በበኩላቸው በ2011/12 የምርት ዘመን 23 ኩንታል ምርጥ ዘር በማምረት በ34ሺህ 500ብር ሸጠው ገቢያቸውን መሳደጋቸውን ገልጸዋል።

ወደ ምርጥ ዘር ብዜት ከመግባታቸው በፊት 10ሺህ ብር ቆጥረው እንደማያውቁ የገለጹት አርሶ አደሩ በምርጥ ዘር ብዜቱ መሳተፍ በመቻላቸው በአሁኑ ጊዜ በሺህዎች ገንዘብ መቁጠር መጀመራቸውን አርሶ አስረድተዋል።

የቡርቃ አናኒ ቀበሌው አርሶ አደር አብዱላሂ ሐሰን ደግሞ በሁለት ሔክታር መሬታቸው ላይ ያባዙት ምርጥ ዘር በቀዳሚው የምርት ዘመን የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ አግዟቸዋል።

በዚህም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመተጋገዝ ካመረቱት 82 ኩንታል ምርጥ ዘር ሽያጭ 123ሺህ ብር በማግኘታቸው የተሻለ ተጠቃሚ ስላደረጋቸው ወደፊትም ይሄንኑ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በክልሉ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የምአራብ ቅርንጫፍ ዋና ዳይሬክተር ፉፋ ሾሮ እንዳስታወቁት ለ2012/13 የምርት ዘመን ከ60ሺ ኩንታል የሚበልጥ B.AH 660፤ 661 አና 540 የተባሉ ምርጥ የበቆሎ ዝርያዎችን ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

ኢንተርፕራይዙ ምርጥ ዘር እያባዛ ያለው በክልሉ የተለያዩ ዞኖች በሚገኙ አርሶ አደሮች ፣ በባለሃብቶች እና በመንግስታዊ ተቋማት ማሳ ላይ እንደሆነም ተናግረዋል።

ለተለያዩ የክልሉ ዞኖች እየተሰራጨ የሚገኘው ምርጥ ዘሩ ለምርት ዘመኑ እንዲያገለግል በሚልም በአሁኑ ጊዜ አምስት ሺህ ኩንታል ወደ ምእራብ አርሲ ዞን መጓጓዙን አስረድተዋል።

ከበቆሎ ምርጥ ዘር ተጨማሪ 10ሺ ኩንታል የአኩሪ አተር ፤ የኑግ ፤ የሰሊጥ ፤ ማሽላና ኦቾሎኒ ምርጥ ዘሮች እየተዘጋጁ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም