ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት የወሰድነውን ስልጠና ልንተገብር ተዘጋጅተናል -በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች

77
አዲስ አበባ ሰኔ 22/2010 ''በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመሳተፍ ስልጠና በመከታተላችን ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጁ ነን'' አሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች። ዘንድሮ በአገራዊ አንድነት የወጣቱን ግንዛቤ የሚያዳብሩ ስልጠናዎችና ውይይቶች ለማድረግና በችግር ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማገዝ የሚያስችሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ለመስጠት ታቅዷል። በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ ከተለያዩ ማህበራት የተወጣጡ፣ ከዩኒቨርሲቲ ለእረፍት የተመለሱና በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሰማሩ ናቸው። የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን በአገር አቀፍ ደረጃ ከ13 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ወደተለያዩ አካባቢዎች ለማሰማራት የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል። ወጣቶቹ በየዓመቱ በክረምት በተለያዩ የሥራ መስኮች በመሰማራት ያለምንም ክፍያ ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡበት መርሃ -ግብር ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በደም ልገሳ፣ በአካባቢ ልማትና ችግኝ ተከላ እንዲሁም በመንገድ ትራፊክ ደህንነት አገልግሎቶች ሲሳተፉ ቆይተዋል። ህይወታቸውን በጎዳና ለሚመሩ ወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጠርበትን መንገድ ማመቻቸትን ጨምሮ ወደመጡበት አካባቢ የሚመለሱበትን ስልት መዘየድ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ እየተሳተፉባቸው ካሉ ተግባራት መካከል ናቸው። አረጋዊያንን በመርዳትና በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ ግንዛቤ መስጠትም በወጣቶቹ የሚከናወን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነው። ከዚህ በተጨማሪ በዘንድሮው ክረምት በአገራዊ አንድነት ዙሪያ በወጣቱ ዘንድ ያለው ግንዛቤ እንዲዳብር የሚያግዙ ስልጠናና ውይይቶች እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማገዝ የሚያስችሉ አገልግሎቶች ለመስጠት መታቀዱም ተመልክቷል። ኢዜአ ያነጋገራቸው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ነው የገለፁት። በሎሬት የኪነ-ጥበብ ማሰልጠኛ ተቋም ሥራ አስኪያጅና መምህር ወጣት ናፖሊዮን ዓለሙ በክረምት ወቅት ለሶስት ወራት በተለያየ የኪነ-ጥበብ ትምህርት ዘርፍ መማር ለሚፈልጉ ወጣቶች ተቋሙ ነጻ ትምህርት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ይናገራል። በዚህም እሱን ጨምሮ ሌሎች መምህራንም የበጎ ፈቃድ ስልጠናውን ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ነው ተናግሯል። በወጣቶች ፌዴሬሽን የሴት ወጣቶች ፎረም ሰብሳቢ ወጣት ማርታ ማሞዬ በጎዳና ላይ ያሉ ሴት ወጣቶች ወደተሻለ ህይወት እንዲመጡ የግንዛቤና የድጋፍ ሥራዎችን በማከናወን የበኩሏን ለመወጣት መዘጋጀቷን ገልጻለች። ተማሪ ሳምራዊት ፍቅሬ በበኩሏ የእረፍት ጊዜዋን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማሳለፍ መዘጋጀቷን ገልጻ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ባለው አቅም በሁሉም ዘርፍ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት መረዳዳትን ባህል ማድረግ ይገባል ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች። በተለያዩ ክልሎች ያሉ የወጣቶች ፌዴሬሽኖችም የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችላቸውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል። ከአፋርና ከጋምቤላ ክልሎች የመጡት ወጣት አሊ ሁሴንና ወጣት ሰለሞን አሰፋ በሰጡት አስተያየት ባሉበት አካባቢ በማህበራት የተደራጁ ወጣቶችን በተለያዩ መስኮች በማሰማራት ህብረተሰባቸውን በበጎ ፈቃድ ለማገልገል ዝግጁ ናቸው። አገልግሎቱን በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ለመስጠት ወጣቱ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አስተላልፈዋል። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አገር አቀፍ  የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ረቂቅ ፖሊሲ በማዘጋጀት አገልግሎቱ በፖሊሲ እንዲደገፍ እየሰራ መሆኑን ኢዜአ ከሚኒስቴሩ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም