በትግራይ ማእከላዊ ዞን የአንበጣ መንጋ ዳግም ተከስቷል

60

አክሱም መጋቢት 03/2012  (ኢዜአ) በትግራይ ማዕከላዊ ዞን አንዳአንድ ቦታዎች ላይ ዳግም የአንበጣ መንጋ መከሰቱን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

በዞኑ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የእጽዋት ክሊኒክና የሰብል ጥበቃ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ረዳኢ በላይ ለኢዜአ እንዳሉት የአንበጣ መንጋው ከየካቲት 28 ቀን 2012 ጀምሮ በዞኑ አብዛኞቹ ወረዳዎች ዳግም ተከስቷል።

ባለፉት አምስት ቀናት በዞኑ ስድስት ወረዳዎች  የተከሰተው የአንበጣ መንጋው  በመስኖ ልማት ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት የመከላከል ርብርብ እየተደረገ ነው ።

 በሁሉም ወረዳዎች መንጋው እንቁላል ጥሎ ለቀጣይ  የመኸር ወቅት ስጋት እንዳይሆን ጭምር ታሳቢ ያደረገ  የመከላከል ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል ።

በላዕላይ ማይጨው ወረዳ የዱራ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር በላይ በየነ እንዳሉት መንጋው በመሰኖ ባለሙት ሰብልና የጓሮ አትክልት  ላይ ጉዳት እንዳያደርስባቸው እየሰጉ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

መንጋው እስከ አሁን ምንም ጉዳት አለማድረሱን ጠቅሰው ሁሉም በባህላዊ መንገድ የመከላከል ሰራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል ።

የሓወልቲ አክሱም እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች ዛሬ መንጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎቸ ከአርሶ አደር ጎን በመሆን የመከላከል ስራ ሲያከናውኑ መዋላቸውን የክለቡ ደጋፊ ወጣት ሳሙኤል ወርቅነህ ተናግሯል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም