በኩታ ገጠም ማልማታችን ለምርታችን የተሻለ ገበያ ለማግኘት አስችሎናል....አርሶአደሮች

93
ሽሬ እንዳስላሴ ሚያዝያ 26/2010 በኩታ ገጠም መሬታቸው ላይ ተመሳሳይ የጓሮ አትክልት በመስኖ ማልማታቸው ለግብርና ምርታቸው የተሻለ ገበያ ለማግኘት እንዳስቻላቸው በትግራይ ክልል የታህታይ ቆራሮና የመደባይ ዛና ወረዳ አርሶአደሮች ገለጹ። ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ የምርት ብክነትን ለመቀነስ እንዳስቻላቸውም አርሶአደሮቹ ተናግረዋል። በታህታይ ቆራሮ ወረዳ "ሰመማ" በተባለ የገጠር ቀበሌ በኩታ ገጠም መሬታቸው ላይ ቀይ ሽንኩርት በመስኖ ካለሙ አርሶ አደሮች መካከል አቶ በዛብህ ረዳኢ እንዳሉት፣  በኩታ ገጠም ማልማታቸው ምርታቸውን በአንድ ጊዜ ሰብስበው ወደ ገበያ ለማቅረብ አስችሏቸዋል፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ ምርታቸውን በጋራ ለሟጓጓዝም ሆነ የተሻለ ዋጋ ለመግኘት እያገዛቸው መሆኑን የገለጹት አርሶአደሩ፣ በበጋው ወቅት በመጀመርያው ዙር በአንድ ሄክታር መሬት ካለሙት ቀይ ሽንኩርት 84 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል። "በተበታተነ መንገድ ለምቶ የተሰበሰበን የጓሮ አትክልት ጭኖ ለገበያ ለማቅረብ ተሸከርካሪ አይገኝም" ያሉት አርሶ አደር በዛብህ፣  አንዳንዴ ትራንስፖርት ቢገኝ እንኳ ለተወሰን ምርት የሚጠየቅ ዋጋ ከፍ እንደሚል አስረድተዋል፡፡ የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በላይ አበጋዝ በበኩላቸው እንዳሉት የተሟላ የግብርና ማሳዳጊያ ግብአት ተጠቅመው በኩታ ገጠም ካለሙት አንድ ሄክታር መሬት 70 ኩንታል ቀይ ሽንኩር ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ "በኩታ ገጠም መሬት ላይ የጓሮ አትክልት ማልማት ከጀመርን ወዲህ የገበያ ችግር ሳይገጥመን ጅምላ ገዢዎች ማሳችን ድረስ በመምጣት ምርቱን ገዝተው እየወሰዱልን ነው" ብለዋል፡፡ ይህም የትራንስፖርት ወጪያቸውን ከማስቀረት ባለፈ አንድ ኩንታል ቀይ ሽንኩርት በአንድ ሺህ ብር ሒሳብ በመሸጥ የተሻለ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በዞኑ መደባይ ዛና ወረዳ " ባህራ" በተባለ የገጠር ቀበሌ የሚኖሩት ሴት አርሶአደር በረቀች መዝገበ በበኩላቸው፣ በአካባቢያቸው ካሉ ነዋሪዎች ጋር ተመሳሳይ ልማት ማከናወናቸው ከግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ እገዛ በተሻለ ለማግኘት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡ በመስኖ ልማት ተመሳሳይ ምርት በኩታ ገጠም ማምረታቸው የገበያ ተደራሽነታቸውን ከማሳደጉ በላይ ምርታቸውን በጅምላ ለመሸጥና የምርት ብክነትን እንዳስቀረላቸው ገልጸዋል። የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የመስኖ ልማት አስተባባሪ አቶ ሚኪኤለ ተስፋይ ለኢዜአ እንደተናገሩት በዞኑ በበጋው ወቅት በአትክልትና ፍራፍሬ 5 ሺህ 681 ሄክታር መሬት በመሰኖ መልማቱንና ከእዚህም ከ420 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል። ከለማው መሬት ውስጥ 1 ሺህ 450 ሄክታሩ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ የአካባቢውን ስነ ምህዳር መሰረት በማድረግ በሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ቃሪያና በሌሎች የጓሮ አትክልት ዝርያዎች እንዲለማ መደረጉን ነው ያስረዱት፡፡ እንደአቶ ሚኪኤለ ገለጻ አርሶአደሮች በኩታ ገጠም መሬት ላይ ተመሳሳይ ምርት ማምረታቸው በግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ አመቺ መሆኑን ተናግረዋል። ከእዚህ በተጨማሪ አረም ለማስወገድ፣ ለአትክልቱ በጋራ እንክብካቤ ለማድረግና የምርት ግብአት ለአርሶአደሮች በቀላሉ ለማድረስና በአግባቡ ሥራ ላይ ስለማዋላቸው ክትትል ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል። በኩታ ገጠም ማረስ አርሶአደሮችን ለገበያ ተደራሽ በማድረግ በኩልም የራሱ ፋይዳ አለው" ያሉት አስተባባሪው፣ እርስ በርስ እንዲደጋገፉና የልምድ ልውውጥ  እንዲያደርጉ የሚያግዝ መሆኑንም አስገንዘበዋል። በመስኖ ልማቱ ከ6 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተሰታፊ መሆናቸውን አቶ ሚከአሌ አያይዘው ገልጸዋል፡፡
 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም