የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ደርሶበት ከነበረው ጉዳት ሙሉ በሙሉ አገግሟል

166

ጎንደር፣ 03/2012 ( ኢዜአ) በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ባለፈው ዓመት ተነስቶ በነበረው የእሳት ቃጠሎ ጉዳት የደረሰበት አንድ ሺህ ሄክታር የተፈጥሮ ሀብት ሙሉ በሙሉ ማገገሙን የፓርኩ ጽህፈት ቤት ገለፀ ፡፡

በአሁኑ ወቅት የበጋ ሙቀትን ተከትሎ በፓርኩ ላይ ተመሳሳይ የእሳት ቃጠሎ እንዳይከሰት የእሳት አደጋ ተከላካይ ብርጌድ የማቋቋም እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው፡፡

የፓርኩ የህብረተሰብና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ታደሰ ይግዛው ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፈው አመት በእሳት ቃጠሎው ጉዳት የደረሰበት 573 ሄክታር መሬት የጓሳ ሳር በተደረገለት ጥበቃና እንክብካቤ ሙሉ በሙሉ ማገገም ችሏል፡፡

እንዲሁም 467 ሄክታር በሚሸፍነው ውጭና በተባለው ሀገር በቀል የዛፍ ዝርያ ላይ ደርሶ ከነበረው የእሳት ቃጠሎ 90 በመቶ የሚሆነው የዛፍ ዝርያ በአጭር ጊዜ መልሶ ማገገም መቻሉን ገልፀዋል።

የፓርኩ የተፈጥሮ ሀብት በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ማገገም መቻሉ መኖ ፍለጋ ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች ሄደው የነበሩ የፓርኩ የዱር እንስሳት ዳግም ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

የዋልያና የጭልዳ ዝንጀሮዎች ዋና የመኖ ምንጭ የሆነው የጓሳ ሳር ሙሉ በሙሉ ማገገም መቻሉ የዱር እንስሳቱን ደህንነት ለማስጠበቅ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ሃላፊው ገልጸዋል፡፡

የፓርኩን ስነ-ምህዳር ለመጠበቅ ባለፈው ክረምት በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ38 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰው በተደረገው ጥበቃና እንክብካቤ 68 በመቶ ያህል ሊፀድቅ እንደቻለ ተናግረዋል።

በፓርኩ ክልል በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ አደጋ ሊከሰት የሚችለውን የእሳት ቃጠሎ በፍጥነት መቆጣጠር የሚያስችል አንድ የእሳት አደጋ ተከላካይ ብርጌድ የማቋቋም ስራ እየተካሄደ እንደሆነም አቶ ታደሰ አስታውቀዋል።

18 ለሚሆኑ የእሳት አደጋ ተከላካይ ብርጌድ አባላት በፌደራል የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን በዘመናዊ የእሳት አደጋ መከላከል ሙያ ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

ለአባላቱም እሳት መቋቋም የሚችሉ ልዩ ልዩ አልባሳት ከአለም አቀፉ የትምህርት የሳይንስ የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ /በድጋፍ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡  

የፓርኩን ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ፓርኩን ከሚያዋስኑ 5 ወረዳዎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ 10 አባላት ያሉት ተንቀሳቃሽ ቡድን ተቋቁሞ ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓል፡፡

በደባርቅ ከተማ የሚገኘው የቱሪዝም ልማትና ግብይት ህብረት ስራ ዩኒዮን ሊቀ-መንበር ቄስ ሞገስ አየነው በበኩላቸው ከቱሪዝሙ ተጠቃሚ የሆኑ ሰባት ሺህ  የሚሆኑ የዩኒዮኑ አባላት በፓርኩ ጥበቃና ልማት የበኩላቸውን ድጋፍ እያደረጉ ናቸው፡፡

አባላቱ በፓርኩ ክልል ችግኝ በመትከል፤ የዱር እንስሳቱን ከህገ-ወጥ አደን በመከላከል ተሳታፊ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

412 ስኩዮር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ፓርኩ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት / ዩኔስኮ/ በአለም የተፈጥሮ ቅርስነት መመዝገቡ ይታወቃል።

ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ፤ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ ስፍራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም