''ነጋሪ'' መጽሔት አነጋጋሪ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጽሁፎችን ይዛ ወጥታለች

86

 አዲስ አበባ (ኢዜአ) መጋቢት 2/2012 በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የምትዘጋጀው ''ነጋሪ'' መጽሔት አነጋጋሪ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዛ ወጥታለች።

መጽሔቷ በአራተኛ ዓመት ቁጥር 11 ዕትሟ ከያዘቻቸው ጉዳዮች መካከል በጥላቻ ንግግርና የሐሰት ማስረጃ፣ ሲቪል ሰርቪስ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የቱሪዝም ልማት ዓበይት ጉዳዮች ናቸው።

''በሩ ገርበብ ይበል!'' የሚል የሽፋን ርዕስ ያገኘው ጉዳይ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው ዓዋጅ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ምሁራንንና ጋዜጠኞችን ያነጋገረችበት ጽሁፍ ነው።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ የሚተነትን ጽሁፍ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስን አነጋግራለች።

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴንና አምራቾችን ያካተተው ትንታኔም በቀጣዩ የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና በተለይም የስንዴ ልማት በመጽሔቷ የተስተናገደ ሌላው ርዕሰ ጉዳይ ነው።

''ባለ ዘውድ ቅርጹ የዓለም ስጋት'' በሚል ርዕስ ዝርዝር መረጃ የቀረበበት የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ጉዳይም በመጽሔቷ ሽፋን ካገኙት መካከል ሆኗል።

የኢትዮጵያን የቱሪዝም እንቅስቃሴና ከአፍሪካ ኅብረት ታሪክን የሚመለከቱ ጽሁፎችም በመጽሔቷ ተካተዋል።

''ነጋሪ'' በጥናትና ምርምር ላይ ያተኮረ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ትንታኔና በሞጋች ሐሳቦች የዳበሩ ጽሁፎች የሚቀርቡባት የኅትመት ውጤት ናት።

መጽሔቷ ምሁራንን፣ ተመራማሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ የመንግሥት አስፈጻሚዎች፣ ሲቪክ ማህበራትና የመንግሥት ሠራተኞችን ተደራሽ ታደርጋለች።

ማሳወቅን ዋነኛ ዓላማ ያደረገችው ''ነጋሪ'' መጽሔት ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በኅትመት ላይ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም