በህጻናት ማሳደጊያ ማዕከላት የሚገኙ ታዳጊዎች ህክምናን ጨምሮ ተገቢውን እንክብካቤ እንደማያገኙ ጠቆሙ

95
አዲስ አበባ ሰኔ 22/2010 በህጻናት ማሳደጊያ ማዕከላት የሚገኙ ታዳጊዎች ህክምናን ጨምሮ ተገቢውን እንክብካቤ እንደማያገኙ ተናገሩ። በአፍሪካ ለ28ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ27ኛ ጊዜ “ህጻናትን ከጎዳና ህይወት እንታደግ” በሚል መሪ ቃል ሲከበር የቆየው የአፍሪካ ህጻናት ቀን በዓል የማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሄዷል። በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙና አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ህጻናት እንደተናገሩት ለህጻናት ድጋፍና እንክብካቤ በሚሰጡ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት የሚታዩ ክፍተቶች ሊታረሙ ይገባል። በህጻናት ማሳደጊያ ማዕከላት የሚኖሩት የ15 አመት ታዳጊ ህጻናት የሆኑት ህጻን በለጡ ተሾመ እና  ዊንታና ብዙአየሁ  በማዕከላቱ የልብስ፣ መጠለያ፣ የትምህርት መሳሪያዎችና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸው ቢሟሉላቸውም የንጽህና መጠበቂያ ዕቃዎች እጥረት፣ ከምግብ አዘገጃጀት ንጽህና ጉድለት፣ የተሟላ ህክምና አገልግሎት በማግኘት ረገድ ችግሮች እንዳሉባቸው ጠቁመዋል። በንጽህና ጉድለት ሳቢያም በርካታ ህጻናት ለህመም እንደሚዳረጉና በአፋጣኝ የህክምና አገልግሎት እያገኙ እንዳልሆነ ለኢዜአ ተናግረዋል። የህጻናቶቹ አሳዳጊዎች ችግሮቻቸውን ለማዕከላቱ ሀላፊዎች በፍጥነት በማሳወቅ እንዲፈታ የሚያደርጉት ጥረት አነስተኛ መሆኑንም ገልጸዋል። ህጻን በለጡ ተሾመ በማዕከሉ ህጻናት በሚታመሙበት ወቅት ቶሎ ህክምና እንደማያገኙ  ትናገራለች። ህጻን ዊንታና ብዙአየሁ በበኩሏ የማዕከሉ ሀላፊዎች የቅርብ ክትትል እንደማያደርጉና የህጻናቶቹ አሳዳጊዎች ሀሳብ ብቻ እንደሚቀበሉ ገልጻለች። ህፃናቱ ማዕከላቱን የሚከታተሉ ባለ ድርሻ አካላት ድንገተኛ ጉብኝት በማድረግ ክፍተቶቹ እንዲታረሙ እንዲያደርጉላቸውም ጠይቀዋል። የ13 አመት ዕድሜ ያላቸው ህጻን ትንሳኤ ተሾመና የማርያም ግርማ  በበኩላቸው ሕብረተሰቡ ለችግር የተጋለጡ ህጻናትን ለመደገፍ የሚያደርገው ጥረት በተደራጀ መልኩ እንዲሆንና ህጻናት ለሱስ እንዳይጋለጡ ግዴታውን መወጣት እንደሚገባ ተናግረዋል። በሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር የህጻናት ድጋፍ አገልግሎት ኢንስፔክሽን ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ገብረአብ በህጻናት ማሳደጊያ ማዕከላት መደበኛና ድንገተኛ ጉብኝት በማድረግ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። በክትትል ወቅት የጐላ ችግር የታየባቸው ማዕከላት ላይ በቂ መረጃ በማሰባሰብና ጥናት በማድረግ ከበጎ አድራጎት ማህበራት ኤጀንሲ ጋር በጋራ በመስራት እንዳይቀጥሉ እንደሚደረግ ገልጸዋል። እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለጻ፤  ሚኒስቴሩ ከበጎ አድራጎት ኤጀንሲ ጋር በጋራ በርካታ ችግሮች ያሉባቸው የማሳደጊያ ተቋማት ላይ ጥቆማና የተሟላ መረጃ ከተገኘ አፋጣኝ እርምጃ ይወሰዳል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም