ሦስተኛው ‘ሶልቭ አይቲ 2020’ የተሰኘው የፈጠራ ሥራ ውድድር ተጀመረ

69

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2012 (ኢዜአ) የወጣቶችን የቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራ ለማበረታታት የሚካሄደው የ'ሶልቭ አይቲ 2020' ውድድር መርሃ ግብር ተጀመረ። 

የውድድር መርሀ ግብሩ የአሜሪካ ኤምባሲ ከጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ጋር በመሆን ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማበረታታት የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።

ዘንድሮ በሚካሄደው ውድድር በተለያዩ ዘርፎች ቴክኖሎጂ ነክ የፈጠራ ክህሎት ያላቸው ዕድሜያቸው ከ19 እስከ 28 ዓመት የሆኑ ወጣቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል።  

ወጣቶች ያሏቸውን ክህሎትና እውቀት በሶልቭ አይቲ 2020 ይፋዊ ድረ-ገጽ ላይ በመመዝገብ ለአንድ ዓመት በሚካሄደው ውድድር ተሳታፊ መሆን እንደሚችሉም ተጠቁሟል።

በውድድሩ አሸናፊ ለሆኑ ግለሰቦች የራሳቸውን የቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራ ለማጎልበት የሚያስችላቸው የገንዘብና የሙያዊ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ታውቋል።   

በውድድሩ በርካታ ወጣቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ በአገሪቱ በተመረጡ 15 ከተሞች በስፋት የማስተዋወቅ ሥራ ከዛሬ ጀምሮ ይሰራል ተብሏል።

የሶልቭ አይቲ 2020 ፕሮጀክት ማናጀር ወይዘሪት ቤዛዊት ካሳዬ እንደተናገሩት ውድድሩ የሚካሄደው በአገሪቱ የፈጠራ ሥራን ለማበረታታትና ለማስፋፋት ነው።

በአገሪቱ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት በአመዛኙ በከተሞች አካባቢ የተወሰነ መሆኑን ገልጸው፤ ውድድሩም የቴክኖሎጂ ስርጭቱን ለማስተካካል እንደሚረዳ አመልክተዋል።

ከዚህም ጎን ለጎን በአገሪቱ የሚስተዋለውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ የሚደረገውን አገራዊ ጥረት በማገዝ በኩል የራሱ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም