አንድነት ፓርክ የኢትዮጵያን ህብረ ብሔራዊ እሴት በግልጽ ያሳያል

142

አዲስ አበባ  መጋቢት 2/2012 (ኢዜአ) አንድነት ፓርክ ኢትዮጵያ የህብረ ብሔራዊ እሴት ባለቤት መሆኗን በግልጽ እንደሚያሳይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ መካከለኛ አመራሮች ተናገሩ።

አመራሮቹ ፓርኩን በማህበራዊ ሚዲያ ከሚሰሙት በተለየ መልኩ እንዳገኙትም ነው ጨምረው የገለጹት።

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ለ15 ቀናት ሲሰጥ የነበረው የብልጽግና ፓርቲ መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ተጠናቋል።

ስልጠናውን ሲከታታሉ የነበሩ አመራሮችም ዛሬ አንድነት ፓርክን ጎብኝተዋል።

ሰልጣኞቹ በቆይታቸው ለቀጣይ የኢትዮጵያ ብልጽግና አሻራቸውን እንዲያስቀምጡ የሚያስችሏቸውን ልምዶች መቅሰማቸውን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ አገረ መንግስት ግንባታ ሂደት፣ የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም እንዲሁም በተጀመረው አገራዊ ለውጥ  የኢትዮጵያ ብልጽግና እንዴት ይረጋገጥ የሚሉ ሃሳቦች ደግሞ በስልጠናው ትኩረት የተሰጠባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል።

አንድነት ፓርክ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ወዴት እየተጓዘች እንደሆነ እንደሚያመላክት ጠቁመዋል።

ፓርኩ የኢትዮጵያን ብዝሃ ሃይማኖት፣ ባህልና ቋንቋ እንደሚያሳይም ገልጸዋል።

ከሰንዳፋ የመጡት አቶ ልማት አሰፋ ስለፓርኩ በማህበራዊ ሚዲያ ከሰሙት የተለየ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸው፤ በተለያዩ አጋጣሚ ወደ መዲናዋ የሚመጡ ዜጎች ፓርኩን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

ከምስራቅ ወለጋ የመጡት ወይዘሪት አልማዝ አመንሲሳ በበኩላቸው በፓርኩ ውስጥ ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝምን እንደተመለከቱ ተናግረዋል።

በፓርኩ የኢትዮጵያን ስርዓተ መንግስት ሂደት፣ ሃይማኖታዊ መሰረት እንዲሁም የብሔር፣ ብሔረሰቦችን ማንነት በታሪካዊ ቅርሶች አስተሳስሮ መያዙን የገለጹት ደግሞ ከጉጂ ዞን የመጡት አቶ አዶላ ዋራ ናቸው።

ጉብኝታቸው ለኢትዮጵያ አንድነትና ብልጽግና አሻራቸውን ለማሳረፍ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱም ያዩትን ታሪክ ለተተኪው ትውልድ እንደሚያስተምሩ በመጠቆም።

ከሰበታ ከተማ የመጡት ወይዘሮ ኬሪያ ከድር "ፓርኩ ቁሳዊ ትውፊትን ጨምሮ ኢትዮጵያ ምን አይነት ገጽታ እንዳላት አሳይቶኛል" ብለዋል።

''የሃይማኖት፣ ብሔርና ሌሎች ልዩነቶች ሳይገድቡን ተቻችለን መኖር እንደምንችል ያስተምራል'' ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም