ዳያስፖራዎች የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር በማስገባትና በማስቀመጥ የጎላ ተሳትፎ እንዳላቸው ተገለጸ

101

ሀዋሳ፣ መጋቢት 1/2012(ኢዜአ) በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባትና በማስቀመጥ የጎላ ተሳትፎ እንዳላቸው ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ያለፉት ስድስት ወራት አፈጻጸሙ ዙሪያ ከባለድርሸ አካላት ጋር በሀዋሳ ከተማ ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ ወቅት የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንዶሰን ግርማ እንደገለፁት ባለፉት ስድስት ወራት በህጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ከገባው አራት ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዳያስፖራው ድርሻ ነው።

እንዲሁም በዚሁ ወቅት 8 ሺህ 807 ዳያስፖራዎች የውጭ ምንዛሪ ተቀማጭ ሂሳብ በመክፈት ከ14 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ሌላ 41 ቢሊዮን ብር ካፒታል አስመዝግበው በንግድና ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ላሳዩ ሁለት ሺህ 570 ዳያስፖራዎች የድጋፍ አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡

ዳያስፖራዎች በህክምና፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በአቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ሀገራቸውን እያገዙ ናቸው።

የኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሠላማዊት ዳዊት በበኩላቸው ባለፉት ስድስት ወራት ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት ፈጥረው ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በተለይ ዳያስፖራው የውጭ ምንዛሪ በህጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ቤት በመላክና ተቀማጭ ሒሳብ በመክፈት የሚያደርገው ተሳትፎ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ዳይሬክተሯ እንዳሉት ተቋርጠው የቆዩ የዳያስፖራው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችም ዳግም እንዲጀምሩ ማድረግ ተችሏል፡፡

በውጭ ሀገራትም እንደዚሁ በቅርብ ወራት ውስጥ የተከናወኑት  ዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

በተለይ በደቡብ አፍሪካና አረብ ሀገራት የኢትዮጵውያን መብት ተጠብቆ የሚኖሩበትን እንዲሁም በእስር ያሉና ጥቃት የደረሰባቸው ዜጎች ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ዳያስፖራዎች በሀገሪቱ በፋይናንስ ተቋማት ላይ መሳተፍ እንዲችሉ የሚያግዝ የህግ ማሻሻያ እንዲደረግም ኤጀንሲው ሁኔታዎች የማመቻቸት ተግባር ማከናወኑንም አመልክተዋል፡፡

በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵውያን የህዳሴው ግድቡን በተመለከተ በገንዘባቸውም ሆነ ዕውቀታቸው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚስችል የማነቃቂያ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡

ከኤጀንሲው ጋር ጠንካራ ቅንጅት ፈጥረው እየሰሩ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳያስፖራ ቅርንጫፍ ሥራአስኪያጅ አቶ ለማ ዋቃዮ ናቸው።

"ዳያስፖራዎችን የተመለከቱ ሥራዎችን የምናከናውነው በመናበብ ስለሆነ ለኛም ትልቅ እገዛ አለው" ብለዋል፡፡

ባንኩ ለዳያስፖራው ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ቅርንጫፍ መክፈቱና በኤጀንሲው ውስጥ ለዳያስፖራው ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል ቢሮ ማመቻቸት መቻሉ በግማሽ የበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ስራዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም