በኢሉአባቦር ዞን ከ88 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሽፈነ

63
መቱ ሰኔ 22/2010 በኢሉአባቦር ዞን ከ88 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኽር እርሻ ዘር መሸፈኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ኢረና እንዳስታወቁት በዘር የተሸፈነው መሬት በ2010/2011 ምርት ዘመን በዞኑ ለማልማት ከታቀደው ከ145 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ ነው። በዞኑ 13 ወረዳዎች መሬቱ በአብዛኛው እየተሸፈነ ያለው በአገዳ፣ ብርዕና የቅባት እህሎች ሲሆን በልማቱም ከ200 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውንና እስካሁንም ከ88 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መልማቱን አስረድተዋል፡፡ የዘር ሥራው ሙሉ በሙሉ በመስመር መዝራት ቴክኖሎጂን በመጠቀም እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው ይህም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። አርሶ አደሮቹ ከቀረበላቸው የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በተጨማሪ በአካባቢያቸው ያዘጋጁትን ከ64 ሺህ ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም 58 ሺህ ሄክታር መሬት አልምተዋል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ተከታታይነት ያለው የሙያ እገዛ በቅርበት እየተሰጣቸው መሆኑንም አመልክተዋል። በዳሪሙ ወረዳ ቤና 01 ቀበሌ አርሶ አደር አብዱረዛቅ ያሲን በሰጡት አስተያየት እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም ሁለት ሄክታር የእርሻ ማሳቸውን በበቆሎ፣ ማሽላና ሩዝ በመሸፈን እየተንከባከቡ መሆናቸውን ገልጸዋል። በመቱ ወረዳ ቡሩሳ ቀበሌ አርሶ አደር ጥላሁን ጉታ በበኩላቸው በግብርና ባለሙያዎችና በግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ድጋፍ በመታገዝ አንድ ሄክታር ማሳቸውን በመስመር መዝራታቸውን ነው የገለጹት። በኢሉአባቦር ዞን ከዘንድሮው የመኸር እርሻ ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱ ታውቋል። ይህም ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ1 ሚሊዮን 100 ሺህ ኩንታል በላይ ብልጫ አለው ተብሏል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም