ከባዕድ ነገር ጋር የተቀላቀለ 36 ኩንታል ዱቄት እና 25 በርሜል ሊጥ በቁጥጥር ስር ዋለ

116

የካቲት 30/3012 (ኢዜአ) በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ስሙ “ጎሮ አደባባይ” በሚባለው አካባቢ ከባዕድ ነገር ጋር ተቀላቅሎ የተዘጋጀ የጤፍ ዱቄትና እንጀራ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የቦሌ ክፍለ ከተማ አስታወቀ።

ከባዕድ ነገር ጋር የተቀላቀለ 36 ኩንታል ዱቄት እና 25 በርሜል ሊጥ፣ 300 እንጀራ እንዲሁም ለእንጀራ መጋገሪያ ሲያገለግሉ የነበሩ 9 የእንጀራ ምጣዶችና ሌሎች ግብዓቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የወረዳው አስተዳደር የምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ውብነህ ዋሴ አስታውቀዋል።

ድርጊቱን ሲፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦች ሕጋዊ የንግድ ፍቃድና የሙያ ማረጋገጫ የሌላቸው መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፣ ኅብረተሰቡ በዚህ ሕገወጥ የምግብ ዝግጅት ምክንያት ከፍተኛ የጤና ችግር እየገጠመው እንደሚገኝና ድርጊቱ ከባህልም አንጻር ያልተለመደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ችግሩ በአንድና በሁለት አካላት ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ ማኅበረሰቡና የሚመለከታቸው አካላት በዚህ ዙሪያ ላይ ጥቆማና ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርጉ አቶ ውብነህ ተናግረዋል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ የምግብ መድሃኒትና ጤና ቁጥጥር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በኃይሉ ዘለቀ፣ ማኅበረሰቡ ቤት በሚያከራይበት ጊዜ የግለሰቦችን መረጃ በአግባቡ በመያዝና ለምን ተግባር እንደሚውል ማወቅና ክትትል ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

ይህንን ሕገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ አካላት ከገንዘብ ይልቅ የኅብረተሰቡን ጤና ታሳቢ በማድረግ ከሕገወጥ ድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን  የዘገበው ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሰክሬተሪ ማህበራዊ ገጽ ያገኘነው መረጃ ሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም