በግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎች በብሔራዊ ፓርኮችና ጥብቅ ስፍራዎች የተደቀኑ ስጋቶችን መቀነስ ተችሏል

93

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30/2012 (ኢዜአ) የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እየተሰሩ ባሉ ሥራዎች በብሔራዊ ፓርኮችና ጥብቅ ስፍራዎች ላይ ለሚታዩ ሰው ሰራሽ ችግሮች መፍትሔ በመስጠት ለውጥ እየመጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

ሰው ሰራሽ ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት አማራጭ የኑሮ ዘዴ መፍጠር ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያሻም ገልጿል።

ኢትዮጵያ 27 ብሔራዊ ፓርኮችና ጥብቅ ስፍራዎች ያሏት ሲሆን ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት 8 ነጥብ 78 ከመቶውን እንደሚሸፍንም መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይግዛው ህገወጥ ሰፈራ በብሔራዊ ፓርኮችና ጥብቅ ስፍራዎች ከሚታዩ ችግሮች ዋንኛው እንደሆነ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በህገወጥ ሰፋሪዎች የደን ጭፍጨፋ፣ ከሰል ማክሰል፣ የማዕድን የማውጣት ሥራ፣ የእርሻ ሥራ ማስፋፋት፣ ልቅ ግጦሽ፣ የእንስሳት ዝውውርና አደን የመሳሰሉ ህገወጥ ተግባርን እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ለተለያዩ ዓላማዎች ለማዋል ደንን የማቃጠል ተግባር እንደሚፈጽሙም አመልክተዋል።

"በዚህ ምክንያት በብሔራዊ ፓርኮችና ጥብቅ ስፍራዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው" ብለዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን ችግር ለመፍታት ባለስልጣኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ብሔራዊ ፓርኮቹና ጥብቅ ስፍራዎች ባሉባቸው አካባቢዎች ህብረተሰቡ ጋር ተከታታይ ውይይት በማድረግ በማህበረሰቡ የተነሳውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጉዳይ መፍትሔ የመስጠት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በህገ ወጥ መንገድ ሰፍረው የነበሩ 230 ሰዎች አማራጭ ቦታ እንዲያገኙ በማድረግ ከፓርኩ እንዲወጡ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ የሚኖረው የበየዳ ማህበረሰብ የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ በፓርኩ የሚገኘውን ደን በመጨፍጨፍ መንገድ ሰርተው እንደነበር ነው አቶ ጌትነት ያስታወሱት።

አሁን ለበየዳ ማህበረሰብ አማራጭ የመንገድ የመሰረተ ልማት በመሰራቱ ከአካባቢው መውጣታቸውን አመልክተው፤ በዚህ ህገወጥ ሰፈራ ምክንያት የፓርኩ ይዞታ ወደ 230 ሄክታር መሬት ዝቅ ብሎ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከህብረተሰቡ ጋር በመስራት የፓርኩን ይዞታ 412 ሄክታር ማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል።

በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ውስጥ የነበረው የከሰል ማክሰል ሥራ ከአካባቢው ማህበረተስብ ጋር በመወያያት እንዲቆም መደረጉን ገልጸዋል።

"በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ በሚጠብቁ ስካውቶች ላይ የሚደረሰውን ግድያ ለማስቆምና የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት የአገር መከላከያ ሠራዊት በሰራው ጸጥታ የማስከበር ስራ ችግሩ ተቀርፏል" ብለዋል።

የአዋሽ፣ ቃፍታ ሽራሮና የአላይደጌ ብሔራዊ ፓርኮች ላይ ለሚታዩ ሰው ሰራሽ ችግሮችም መፍትሔ መበጀቱን ነው አቶ ጌትነት የገለጹት።

በተጨማሪም ህገወጥ የእንስሳት ዝውውርና አደንን ለመከላከልም ከአራት ወር በፊት የአካባቢ የተፈጥሮ ሀብት የወንጀል መከላከል ክፍል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቅሰዋል።

ክፍሉ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና ሌሎች የጸጥታ አካላትን ያካተተ መሆኑን ገልጸው፤ የክፍሉ መቋቋም ህገ ወጥ ተግባራትን በተቀናጀ መልኩ ለማከናወን እንደሚያስችል አመልክተዋል።

የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በተሰሩ ሥራዎች በአጠቃላይ በብሔራዊ ፓርኮችና ጥብቅ ስፍራዎች ለሚታዩ ሰው ሰራሽ ችግሮች መፍትሔ በመስጠት ለውጥ እየመጣ መሆኑን አቶ ጌትነት አመልክተዋል።

"ፓርኮችና ጥብቅ ስፍራዎች ያላቸውን ጠቀሜታ በማስረዳት የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

ሰው ሰራሽ ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት ለህብረተሰቡ አማራጭ የኑሮ ዘዴ መፍጠርና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ትኩረት የሚፈልግ መሆኑን ገልጸዋል።

ፓርኮቹ ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊና ማህበራዊ ጥቅሞች ለማሳደግ ባለስልጣኑ ከሚመለከታቸው አላት ጋር በመሆን በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሁሉም የሚመለከተው አካል በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮችና ጥብቅ ስፍራዎችን የመንከባከብና የመጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣም አቶ ጌትነት ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም