ዩኒዬኖች 26 የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ገነቡ

71

አዳማ፣ የካቲት 30/2012 (ኢዜአ) የህብረት ሥራ ዩኒዬኖች 26 የአግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱሰትሪዎች በመገንባት በግብርና ምርቶቻቸው ላይ እሴት መጨመር የሚያስችል አቅም መፍጠራቸውን የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጄንሲ ገለጸ።

ኤጄንሲው የህብረት ሥራ ሴክተሮች የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የሥራ እቅድ አፈፃፀም በአዳማ ከተማ እየገመገመ ነው።

የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጄንሲ የእቅድና የህብረት ሥራ ልማት ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብዲ አደም እንደገለፁት ባለፉት ስድስት ወራት 26 የአግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ተገንብተው የግብርና ምርቶች የማቀነባበር ሥራ በማከናወን ላይ ናቸው።

በአማራ፣ ኦሮሚያና ትግራይ ወደ ሥራ ከገቡት የአግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የወተትና ወተት ተዋፅእኖ ፣ ማርና ሰም፣ ቅመማ ቅመምን ጨምሮ የዘይት ማቀነባበሪያዎች ይገኙበታል።

የህብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒዬኖች በተጨማሪም ከ22 ሺህ ቶን በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ግብይት ማከናወናቸውን ጠቅሰው በማህበራቱ በኩል ወደ ውጭ ከተላኩት የግብርና ምርቶች ከ35 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ በግማሽ ዓመት መገኘቱንም ተናግረዋል።

ለ22 የህብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች ማጠናከሪያ  2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ብድር መሰራጨቱን የገለጹት አቶ አብዲ አደም ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ መቆጠባቸውን ገልፀዋል።

የኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ሱሩር እንደገለፁት የህብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒዬኖች የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር በአግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ልማት ግንባር ቀደም ሚና እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሰራ ነው።

በተለይ የግብርና ሴክተሩን በማዘመን ረገድ፣ ምርትና ምርታማነትን በእጥፍ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችና የመካናይዜሽን አገልግሎት በማስፋፋት ረገድ ድርሻቸው የላቀ መሆኑን አመልክተዋል።

ምርታማነቱን ከማሳደግ ባለፈ ምርቱ በእሴት ሰንሰለት ውስጥ እንዲያልፍ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ግብይት ያላቸው ተሳትፎና የውድድር አቅም ማጎልበት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫችን ነው ብለዋል።

በአቅርቦት፣ በጥራት፣ በአቅምና በፋይናንስ አገልግሎት፣ በኦዲትና ቁጥጥር፣ በግብይት ብቃት ያለባቸውን ክፍተት ለመሙላት ጭምር እየተሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጠዋል።

በዚህም ለሀብት ብክነት የተጋለጠውን የውስጥ አሰራራቸውን ከመሰረቱ ለመለወጥ፣ ብቃት ባለው የሰው ሃይል ማደራጀትና የቴክኖሎጅ አጠቃቀም አቅማቸውን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአዳማ ከተማ ዛሬ በተካሄደው መድረክ ላይ ከዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች የተወጣጡ የህብረት ሥራ ዘርፍ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ታሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም