የሚገናኛ ብዙሃኑ ኢንዱስትሪ በባለሙያዎች እንዲመራ አስገዳጅ መመሪያ ተዘጋጀ

72

የካቲት 30/2012 ዓ.ም (ኢዜአ) የሚዲያ ፍቃድ የሚሰጠው ለሙያው ቅርበት ላላቸው ባለሙያዎች ብቻ እንዲሆን የሚያስገድድ መመሪያ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ የምስራቅ አፍሪካ የሚዲያ ስልጠና ማዕከልን ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ገልጿል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዱአለም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሚዲያ ኢንዱስትሪው  ከንግድ ዘርፍ ኢንቨስትመንት መለየት አለበት።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር ማንኛውም ባለሃብት ወደ መገናኛ ብዙሃን ኢንዱስትሪው ለመቀላቀል በሚያቀርበው ጥያቄ መሰረት ብቻ ፈቃድ ያገኝ ነበር።

ይሁንና ተቋማቱ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ከአመራሩ ጀምሮ በሚዲያው ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያዎች ሙያዊ ብቃት ያላቸው መሆን እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

አዲስ በተዘጋጀው መመሪያ የመገናኛ ብዙሃንን ለማቋቋም ፈቃድ የሚጠይቁ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ከሙያው ጋር ያላቸው ግንኙነትና የሥራ ልምዳቸው ጭምር ግምት ውስጥ እንዲገባ የሚያስገድድ ሃሳብ በመመሪያው ውስጥ እንዲካተት መደረጉን አቶ ወንድወሰን ተናግረዋል።

መመሪያው የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ገንዘብን ብቻ ታሳቢ አድርገው እንዳይሠሩና ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ የሚያስችል እንደሚሆንም አስረድተዋል።

"ባለስልጣኑ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ባለሙያዎችን ሙያዊ አቅም ለማሳደግ ተከታታይ የሥራ ላይ ስልጠናዎች የሚያገኙበት ማዕከል ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ ነው" ብለዋል።

ማዕከሉ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚዲያ ስልጠና አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

የስልጠና ማዕከሉን ለመገንባት ንድፈ ሀሳብ ተቀርጾ  ከኳታር መንግስትና ከአልጀዚራ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱንም አመልክተዋል።

ይህ የስልጠና ማዕከል ለሁሉንም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት አቅም ለመገንባት ተከታታይ ስልጠና የሚሰጥ ነውም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም