ይድረስ ለወይዛዝርት- የዳግማዊ ምኒልክ ደብዳቤዎች

388

አየለ ያረጋል-ኢዜአ

እንደ መንደርደሪያ፡-

ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘ-ኢትዮጵያ በየፈርጁ መተንተን የሚችሉ ደብዳቤዎች አሏቸው። ክብር ለደራሲ ጳውሎስ ኞኞ ይሁንና ደብዳቤዎቹ የአገር ውስጥና የውጭ በሚል በሁለት መጽሐፍት ተሰንደዋል። የንጉሠ ነገሥቱ ደብዳቤዎች ቅርጽና ይዘት ከመደበኛው የመስሪያ ቤት ደብዳቤ አፃፃፍ ስርዓት ይለያሉ-የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከማቋቋማቸው በፊትም ሆነ በኋላ የተጻጻፏቸው። ደብዳቤዎቹ ከአንድ አረፍተ ነገር ጀምሮ አጫጭርና ግልፅ ናቸው። አጫጭር ይሁኑ እንጂ ቅሉ መልዕክታቸውን በሚገባ የሚያስተላልፉ ናቸው። በፈሊጥ አልያም በዘይቤ ለዛ የተዋዙም ናቸው። ደብዳቤዎቹ የአንባቢን ጊዜ፣ የወቅቱን የወረቀት ውድነት የቆጠቡ እንደሆነ በመጽሐፉ መግቢያ የተጻፈው ሀተታ ያስረዳል። ሁሉም ደብዳቤዎቻቸው የንጉሠ ነገሥቱን ትሁት ግለ ባህሪያት እንደሚያንፀባርቁ፤ ንጉሠ ነገሥቱ ያልተስማሙበት ጉዳይ ቢኖርም ስንኳ አሉታዊ መልሶቻቸው ተቀባዩን ቅር እንዳያሰኝባቸው ተጨንቀውና ተጠበው እንደሚያጽፉም የመፃሕፍቱ አርታኢያን መስክረዋል።

በዚህ ጽሁፍ ማንሳት የፈለግሁት ግን ትናንት የካቲት 30 /በፈረንጆቹ ማርች-8/ የተከበረውን የዓለም ሴቶች ቀን በማስመልከት ከሴቶች ጋር የተጻጻፏቸውን ደብዳቤዎች በወፍ በረር ለማንሳት ነው።

የሴቶች ቀን ሲከበር

በርግጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ሴቶች ወደ ዘመናዊ የልማት አውታሮች ተሳትፎ መነሳሳት የጀመሩት ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ጀምሮ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። ንጉሡ በደብዳቤዎቻቸው ከሚያንጸባርቁት መልዕክት በተጨማሪ በድርጊትም ለሴቶች ያላቸውን ክብርና የመብት ተቆርቋሪነት ያሳዩ ናቸው። ነገሥታት ልጆቻቸውን ከመውለዳቸው በፊት ጀምሮ ፖቲካዊ  ጋብቻ የተለመደ ነው። /በእኔ እምነት የመኳንንትና የንጉሳዊያን ቤተሰብ ሴቶች በተድላ በፍስሐ እንደሚኖሩ ቢገመትም ዳሩ እንደ ዘመናችን ባለስልጣናት ልጆች እንዳሻቸው የሚፈነጩ ሳይሆን በቤተሰብና ከጋብቻ እስከ ማኅበራዊ ሕይወት ነጻነትን የተነፈጉ፣ ግለ ሕይወታቸውን የማይኖሩ ጭቁኖች ናቸው በብዛት። ይህን የሚያሳዩ የበርካታ ልዕልታትን ታሪክ ማስታወስ ይቻላል/።

ዳግማዊ ምኒልክ ገና የሸዋ ንጉስ በነበሩበት ጊዜ ከንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ጋር የነበራቸውን ባላንጣነትና ፖለቲካ ለማርገብ ልጃቸውን ዘውዲቱን የ12 ዓመት ታዳጊ ለነበሩት ለአፄ ዮሐንስ ልጅ ለራስ አርዓያሥላሴ እንዲሰጡ የተጠየቁት ዘውዲቱም ገና የስድስተ ዓመት ህጻን ሳለች ነበር። አላቻ ጋብቻ በነገስታቱ ዘንድ የተለመደ ቢሆንም ንጉስ ምኒልክ ግን ልጅቷ ለወግ አልበቃችም በሚል ተቃውመው እንደነበር ፀሃፊ ትዕዛዝ ገብረስላሴ ዘግበዋል። ምንም እንኳን 'ልጅህ ልጃችን ናት እኛ እናሳድጋለን' በሚል በአጼ ዮሐንስ ተፅእኖ ምኒልክ ሳይወዱ ብትዳርም። በኋላም የራስ አርዓያስላሴን ሞት ተከትሎ ዘውዲቱ ደጃዝማች ውቤ አጥናፍሰገድን አግብታ ነበር። አንድ ቀን ደጃች ውቤ የንጉሱን ልጅ ባለቤታቸውን ዘውዲቱን በጥፊ ስለመቷት ዘውዲቱ ከደጃች ውቤ /ጊዮርጊስ/ ወደ ታላቁ ቤተ መንግስት /አራት ኪሎ/ ተንከብክባ በመሄድ ምኒልክ ፊት አለቀሰች። ምኒልክም የልጃቸውን ባል ጠርተው 'ምነው መታኸኝ' በሚል 'በጥፊ አጩለው ሰደዱት፤ ዘውዲቱም በዛውት ፍቺ ፈጸማ ቀረች' ይባላል። እንኳንስ ለፖለቲካ ጋብቻ ይቅርና ሚስቶች አካላዊ ድብደባ እየደረሰባቸው ከባሎቻቸው እንዲለምዱ በሚገደዱበት ባሕል ምኒልክ ግን ልጃቸውን ልመጅ ከማለት ይልቅ ጥቃት የፈጸመውን አማቻቸውን በመቅጣት ለሴቶች ያላቸውን ክብር በልጃቸው አሳይተዋል። ምናልባትም ዳግማዊ ምኒልክ ከሕዝብ ተወዳጅነታቸው በተጨማሪ ለሴቶች ባላቸው ክብርና ተቆርቋሪነት ሊሆን ይችላል 'እምዬ' በሚል ቅጽል ስም የተጠሩ ብቸኛው የኢትዮጵ ንጉስ የሆኑት።

አሁን 'አጤ ምኒልክ በሐገር ውስጥ የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች' በሚለው የጳውሎስ ኞኞ መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱ ጥቂት ደብዳቤዎችን ላውሳ። ከሁሉም በፊት ግን በግንቦት 6 ቀን 1899 ለእቴጌ ጣይቱ የተላከውን ላስቀድም።

"ይደረስ ለእቴጌ ጣይቱ

ብርሃነ ዓለም ዘተሐርየት ላክዊት ብእሲት ወእም

እንዴት ውለሻል። እኔ እግዚአብሄር ይመስገን ደህና ነኝ። እኔም በዚሁ በሰረገላ ደህና ገባሁ። ከሰረገላው መንገድ ይልቅ ከዚሁ በድንጋይ የተበጀው ይህ መልካም መንገድ ነው። ነገር ግን የራስ ወልዴ ነገር ጧት ዘንግቸው ሳልጠይቅ መጣሁ። አሁንም በጎ መሆኑን ሁሉንም እንድታስታውቁን ይሁን"

ሰኔ 21 ቀን 1898 ዓ.ም ወይዘሮ ላቀች (ምናልባትም የራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ልጅ) ለተባለች ወይዘሮ የላኩት ደብዳቤ ሰብዓዊነት ያለው፣ ቅንነት የተሞላበት፣ ብርታት የሚሰጥና በዘይቤ የተዋዛ ነው።

"አሞሻል ማለትን ሰማሁ። አሁን ጦሙን ገድፈሽ በቶሎ ብትድኚ አይሻልም። ይህ ማለቴ ይህቺ ለፍተሽ ያሳደግሻት ልጅ ለቁም ነገር እስክትደርስ ድረስ ጥቂት ቀን እንኳ ብትቆይላት ብዬ እንጂ ያንቺማ ነገር ምንግዜም ቀርቷል። እንግዲህ ዘመድ አትሆኝንም። አሁንም በጦሙ ግደፊልኝ"

ወይዘሮ ዘውዲቱ ደስታ ለተባሉ በቅሎ ለተቃጠለባቸው ሴት ጥር 30 ቀን 1898 ዓ.ም የላኩት ደብዳቤ ደግሞ እንዲህ ይነበባል። እርቅ ምን ያህል እንደሚወዱም በተመሳሳይ ዓመት የካቲት 20 ቀን 1898 ዓ.ም የጻፉት ደብዳቤ ይመሰክራል።

"በቅሎ ተቃጠለኝብሽ ማለትን ሰማሁ። አንቺ ግን መቸም አትወጂኝም። በቅሎ ተቃጠለብኝ ብለሽ ሳትልኪብኝ ቀረሽ። የአፈ ንጉስ ነሲቡ በቅሎዎች ሁሉ ተቃጥለው ከእኔም ነገር ሰርቶ የወሰደው ግራጫ በቅሎ ተቃጥሎ የሚሄድበት በቅሎ አጥቶ እየታዘለ ቢመጣልኝ እወድ ነበር። አሁንም ማለፊያ በቅሎ ሰድጀልሻለሁ። ለአፈ ንጉስ ነሲቡ ያዋስሽ እንደሆነ እንኳን በቅሎዋን አገሩንም እወስድብሻለሁ። ኮርቻ ግን አለመጨመሬ ኮርቻ አልተቃጠለብሽም ብዬ ነው"

በተመሳሳይ የካቲት 20 ቀን 1898

"የሰደድሽልኝን ደብዳቤ አየሁት። ነገር ግን ደብዳቤው ሳትታረቁ አስቀድሞ የተጻፈ ነው። አሁን መታረቃችሁን በስልክ ሰምቸ ደስ አለኝ"

ሴቶች ሲቸግራቸው እምዬ ምኒልክን እንደሚጠይቁና እርዳታ እንደሚለገሳቸው ይህ ለወይዘሮ መነን /ምናልባት የኋላዋ እቴጌ መነን አስፋው ልትሆን ትችላለች/ በታህሳስ 15 ቀን 1898 ዓ.ም የተላከ የሁለት ዓረፍተ ነገር ደብዳቤ ያረጋግጣል።

"ይድረስ ለወይዘሮ መነን

ደብዳቤሽም ደረሰኝ። መቶ ብር ሰድጀልሻለሁ"

የወይዛዝርቱ ደህንነትና ክራሞት ያሳሰባቸው ንጉሱ ቤተሰባዊ ደብዳቤዎችን ከመላክ አልተቆጠቡም።  ተከታዩ ደብዳቤ ወይዘሮ ምንትዋብ /የራስ ወሌ ብጡል ልጅ?/፣ ወይዘሮ ሙሉእመቤት፣ ወይዘሮ አሰለፈችና ወይዘሮ አማረች ለተባሉ ወይዛዝርት እንደ ቅደም ተከተላቸው የሚከተሉትን ደብዳቤዎች በተመሳሳይ ዓመት /1898 ዓ.ም/ ልከዋል። እንዲሁም በ1899 ወይዘሮ የሺመቤት፣ ወይዘሮ ንግስት፣ ወይዘሮ አስካለማርያም ለተባሉ ወይዛዘርት ተመሳሳይ ይዘት ያለው ደብዳቤ ልከዋል።

ለወይዘሮ ምንትዋብ

"የጤንነትሽ ነገር የላክሽውን ደብዳቤ አይቸ ደስ አለኝ። ደግሞ እግዚአብሄር በደህና አክርሞ በሕይወት ለመገናኘት ያብቃን"

ለወይዘሮ ሙሉእመቤት

"በደህና መገላገልሽን የላክሽው ደብዳቤ ደረሰኝ። እንኳን ማርያም ማረችሽ። እግዚአብሄር በደህና አክርሞ በሕይወት ለመገናኘት ያብቃን"

ለወይዘሮ አሰለፈች

"አገሩንስ ለመድሽው እንደምንድነሽ። ፊትስ አሞሻል ማለትን ሰምተን አስደንግጠሽን ነበር። በኋላ ግን በጎነትሽን ብሰማ እጅግ ደስ አለኝ። ደግሞ እግዚአብሄረ በደህና አክርሞ ለመገናኘት ያብቃን"

ለወይዘሮ አማረች

"ደህንነትሽን የላክሽው ደብዳቤ ደረሰኝ። ደግሞ እግዚአብሄር በደህና ለመገናኘት ያብቃን"

የሴቶች ሃብት ንብረት በፍትሃዊነት የመካፈል መብታቸው እንዲጠበቅ በተለያዩ ደብዳቤዎች ትዕዛዝ ሰጥተዋል። ለምሳሌ በ1899 ዓ.ም ፊታውራሪ ተሰማና ግራዝማች ወልደዮሐንስ ለተባሉ ባለሟሎቻቸው የላኩት ደብዳቤ ወይዘሮ ጥሩወርቅ የተባሉ የራስ በዛብህ ተክለሃይማኖት ልጅ ሀብት እንድትካፈል አዝዝዋል።

"የራስ በዛብህ ልጅ ጥሩወርቅ ገንዘቤን ልካፈል ብል ከለከሉኝ ብላ ብትጮህልኝ ትካፈል ብዬ ወደ ወንድሟ ላኩ አልኩ እንጂ ወደ እናንት ፃፉ አላልኩም ነበር። የቀንድ ከብቱንም ከብት ለሌለው ድሃ ስጡ ብለናል። ከቀንድ ከብት በቀር ሌላ ምን ገንዘብ ይኖር ይሆን"

ከንብረት ክፍፍል አልፈው ከትዳር ጋር የተያያዙ አስገራሚ ደብዳቤዎችንም ጽፈዋል። ወይዘሮ ንግስት የምትባል የንጉስ ተክለሃይማኖት ልጅ፤ የዳሞቱ ገዥ የራስ ቢትወዳድ መንገሻ አቲከም ልጅ ደጃዝማች መርዕድ መንገሻና የጣይቱ ብጡል እህት ልጅ ደጃች ገሠሠ የተባሉ /የእቴጌ ጣይቱ አክስት ልጅ/ የስሜንና ወልቃይት ገዥ 'እኔ ላግባ እኔ ላግባ' በሚል ተጣሉ። ወይዘሮ ንግስትም የጎጃምና የጎንደር መኳንንት ጦር ሲማዘዙባት ምኒልክን 'ማን ላግባ' ደብዳቤ ላኩላቸው። እምዬ ምኒልክም 'የወደድሽውን አግቢ' ብለው ምላሽ ሰጡ። ንግስትም ደጃች ገሰሰን አገባች። ተከታዩ ጥቂት ደብዳቤም /ለደጃዝማች ገሠሠና ለደጃዝማች ይግዛው በተመሳሳይ ቀን ጥር 3 ቀን 1899 ዓ.ም የተጻፈው/ ይህን ያሳያሉ። በጥር የተዳረችውን ሙሽራ ሰኔ ወር ላይ ሙሽራዋ ከባሏ አገር እንኳን በደህና ደረስሽ ብለዋታል።

"ይድረስ ከደጃች ገሠሠ

መኳንንቶች የወይዘሮ ንግስትን ነገር ጠይቀው ነበር። ቀድሞም ቢሆን እሺ የፈቀድሺውን ታግባ ብዬ ነበር። እሷ ግን ደጃች ገሠሠን አገባለሁ ብላ ብትልክልኝ ግራዝማች ወልደዮሐንስን አባት ሆኖ አፈጣጥሞ ይስጥ ብዬ ልኬያለሁ"

"ይድረስ ከደጃዝማች ይግዛው

ወይዘሮ ንግሥት ደጃዝማች ገሠሠን አግብታ ወደ ስሜን ትሄዳለችና አንተ አገር ሲደርሱ መጠን እያዘዝክ ያንተን አገር አስኪያልፉ ድረስ መስተንግዶ እያገባህ እየሸኘህ እንድትሰዳቸው ይሁን። ለፊታውራሪ መሸሻም በዚሁ ቃል ተጽፏል"

"ይድረስ ከወይዘሮ ንግሥት

በደኅና መግባትሽን በላክሽልኝ ደብዳቤ አየሁት። እንኳን ደኅና ገባሽ"

ዳግማዊ ምኒልክ ለወይዛዝርቱ የላኩት ማጽናኛውን ብቻ ሳይሆን በህመም ወቅት ለፈውስ የሚሆን ምክራቸውን ጭምር ነው። ለምሳሌ ለወይዘሮ አሰለፈች /ምናልባት የእቴጌ ጣይቱ ቤተሰብ አሰለፈች ወንዴ?/ ምክርና መጽናኛም ልከዋል-የመድሃኒት ትዕዛዝ ሰጭ ሃኪም ሆነዋል ማለት ይቀላል። /እቴጌ ጣይቱ ለዙፋን ማረጋጊያ ዘመዶቻቸውን ለተለያዩ ባላባቶች መዳር ያዘወትሩ የነበረ ሲሆን ወይዘሮ አሰለፈችም በተለያየ ጊዜ ለአራት መኳንንት ማለትም ራስ ልዑልሰገድ፣ ደጃች ይልማ መኮንን /የአጼ ሃይለስላሴ ወንድም/፣ ለልዑል ራስ ሃይሉ ተክለሃይማኖት፣ ለራስ ደምሰው ነሲቡ ድረዋቸዋል። ለወይዘሮ አሰለፈች ከተጻፈው ደብዳቤ ጎን ለደጃች ይልማ መኮንን መታመሙን የሚገልጽ በተመሳሳይ ጊዜ የተጻፈ ደብዳቤ ስላለ በርግጥም ደብዳቤው ባለቤቷ ለታመመባት አሰለፈች ወንዴ ሳይሆን አይቀርም/

በመስከረም 9 ቀን 1900 ዓ.ም

"ለደጃዝማች ይልማ የሳል መድሃኒት ብለሽ የላክሺልኝ ይኸው ሰድጃለሁ። ከዚህ መድሃኒት በጥሪኝ ለክቶ በጥሩ ውሃ ከስኳር ጋር አፍልቶ በሻሽ አጣርቶ በጣም ሳይበርድ ጧትም ቀንም ማታም ቢሆን በትንሽ ኩባያ ወይም በቻይ ፍንጃል መጠጣት ነው.... ደግሞ አንዱ አደራረግ እንዲህ ነው። በለስታ ቅቤ ከዚህ ከመድሃኒት አንድ ጭብጥ ጨምሮ ውሃ ሳይገባበት በቅቤ ብቻ አንጨቅጭቆ አሳድሮ ማለዳ አቅልጦ በማጭመቂያ ጨምቆ ቅቤ እንደሚጠጣ ሁሉ ጧት ጧት በትንሽ ኩባያ ወይም በትልቅ በቻይ ፍንጃል ማጠጣት ነው። ሳሉ እኪለቅ ድረስ። ደግሞም ቅቤው እንዳይሰለች አንድ ቀን በውሃና ስኳር የተፈላውን፣ ደግሞ ሌላ ቀን በቅቤ ብቻ የተጨቀጨቀውን መጠጣት ነው። ሕመሙስ መደበቁ ለምድን ነው። አስቀድሞ ለኛ ማስታወቅ ነበር እንጂ። አሁንም እግዚአብሄር በቀላሉ ያድርግለት"

ጥቅምት 29  ቀን 1900 ዓ.ም /ምኒልክ መድሃኒት ቢልኩም ደጃች ይልማ ከሞት አልተረፈምና ወይዘሮ አሰለፈችን የሚያጽናና ደብዳቤ እንዲህ ጽፈዋል/

"ይድረስ ከወይዘሮ አሰለፈች

የሰደድሽልኝ ደብዳቤ አየሁት። ቀድሞ ነበር እንጂ ማዘን ብዬ የላኩብሽ ፊት አዝነን ያላዳነውን በኋል ከሞተ በኋል ብናዝን እምባ ብናፈስ ምን እናገኛለን ስለማለት ነው እንጂ አንቺ አታዝኝም ለማለት አይደለም። አንቺንም ወደዚህ ነይ ማለታችን በለቅሶው ምክንያት ከፉ ነገር እንዳያገኝሽ ብለን ነው። ለነገሩማ የመታሰቢያ ጠበሉን ዓመቱንስ ብታወጪ እኛ ምን ከፋን ነበር። አሁንስ አርባው ይኸው መድረሱ ነው"

ሲጠቃለል

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከወይዛዝርቱ የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች ከባለቤታቸው ጀምሮ ለሴቶች ያላቸውን ክብር፣ ነጻነት ሰጭና ደጋፊነት ሲያሳዩ ግፍ ለሚያደርሱት ደግሞ ወቀሳ፣ ተግሳጽና እርምጃ ሲሰጡ እንደነበር ይመሰክራሉ። እናም የሴቶች ቀን ሲከበር በእናት ስም "እምዬ" ተብለው የሚጠሩትን ንጉሠ ነገሥትም ማውሳት ተገቢ ነው።

ደራሲ አቤ ጉበኛ አፄ ምኒልክ "እምዬ" የመባላቸውን ምክንያት ፍለጋ ከገጠማቸው ስንኞች ቀንጨብ አድርጌ ላብቃ፡-

እምዬ ምኒልክ ወንድ ነበርክ ወይስ ሴት?

እምዬ ምኒልክ አባት ነበርክ እናት?

እናታቸው ካልሆንህ እንደናት ካላዩህ፤

ትንሹ ትልቁ ለምን እምዬ አሉህ?

ግን ሴት ብዬህ ብቀር ፆታህን ሳላየው፤

ይሰድበኛል ጣልያን ወንድነትህን ያየው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም