የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ማጠናከሪያ የ26 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አደረገ

58

አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2012 (ኢዜአ) የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ "ያልተማከለ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ማጠናከሪያ መርሃ ግብር" የሚውል የ26 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አደረገ።

መርሃ ግብሩ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌና የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንና የአውሮፓ ኅብረት የመርሃ ግብሩን መጀመር በአዲስ አበባ አብስረዋል።

ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ እንዳሉት መርሃ ግብሩ ክልሎች ባልተማከለ አስተዳደር የአደጋ ስጋትን በራሳቸው መቀነስ የሚያስችላቸው ነው።

"ክልሎች ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና እና በሌሎችም ዘርፎች ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመቀነስ ያግዛቸዋል" ብለዋል።  

ኢትዮጵያ የአደጋ ስጋትን ለመከላከል ተቋማዊ እንቅስቃሴ ከጀመረች ከ46 ዓመታት በላይ ማስቆጠሯንም ገልጸዋል።

በአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ የሚደርሰውን ችግር ቀድሞ ለመከላከል መንግስት ፖሊሲ ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል።

ክልሎች ያላቸውን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የአደጋ ስጋትን መከላከልና መቀነስ እንዲችሉ "ያልተማከለ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ማጠናከሪያ መርሃ ግብር መተግበር አስፈልጓል" ብለዋል።

የአውሮፓ ህብረት ለአራት ዓመታት ለሚቆየው መርሃ ግብር የ26 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ በማድረጉም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ዮሐን ቦርግስታም በበኩላቸው አደጋ በማንኛውም ጊዜ ሊደርስ የሚችል በመሆኑ ቀድሞ መዘጋጀት ተገቢ መሆኑን ነው የገለጹት።

"ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የሚቆየው ይሄው መርሃ ግብርም በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ለመከላከል አጋዥ ይሆናል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባልተማከለ አስተዳደር የአደጋ ስጋትን ቀድሞ ለመከላከል ለምታደርገው እንቅስቃሴ የአውሮፓ ኅብረት የሚያደርገው ድጋፍ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

መርሃ ግብሩ ውጤታማ እንዲሆን የሁሉንም ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ የመንግስት ተቋማትም ሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሳተፍ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም