በሜክሲኮ የሴቶች ጥቃትን ለመቃወም በተደረገ ሰልፍ ላይ ግጭት ተከሰተ

102

የካቲት 30/2012 ዓ.ም (ኢዜአ) በሜክሲኮ የአለም የሴቶች ቀን ላይ የሴቶች ጥቃትን ለመቃወም በተደረገ ሰልፍ ላይ ግጭት መፈጠሩን ቢ ቢ ሲ ዘግቧል።

በዘገባው እንደተመለከተው በሜክሲኮ እየጨመረ የመጣውን የሴቶች ጥቃት ለመቃወም ወደ 80 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ወደ አደባባይ ወጥተዋል።

ፖሊስ እንደገለጸው የተቃውሞ ሰልፉ በሰላማዊ ሁኔታ የተጀመረ ቢሆንም አንዳንድ ቡድኖች የፔትሮል ቦንቦችን ወርውረዋል፤ የአገሪቱ ብሄራዊ ቤተ መንግስትና የፕሬዝዳንቱ መኖሪያ በሮች ላይም እሳት አስነስተዋል።

ፖሊስም አስለቃሽ ጋዞችን በመጠቀም ድርጊቱን መከላከሉ ነው የተገለጸው።

በተከሰተው ግጭት ከ60 በላይ ሰዎች መጎዳታቸውና 13 ሰዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተጠቅሷል።

ሰባት ሰዎች በተቃዋሚዎቹ ላይ ጥቃት በማድረሳቸው መታሰራቸው በዘገባው ተመልክቷል።

በሜክሲኮ በየዕለቱ 10 ሴቶች እንደሚገደሉና የአገሪቱ ፖሊስ ከ700 በላይ የሴቶች ግድያ ኬዞችን እየመረመረ እንደሚገኝ ተጠቅሷል።

ሴቶች ላይ አሰቃቂ ጥቃቶችና ግድያዎች እየደረሱ ቢሆንም መንግሰት እርምጃ እየወሰደ አይደለም በሚል ቁጣ መቀስቀሱ ነው የተመለከተው።

በዛሬው ዕለትም ሚሊዮኖች የሚሳተፉበትና እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚደረግ ተገልጿል።

በፓኪስታን የሴቶች ጥቃትን ለመቃወም ሰልፍ በወጡ ሰዎች ላይ ድንጋይና ጫማ መወርወሩ በዘገባው ተጠቅሷል።

በቱርክ ኪይርግያዝታን ከተማ የሴቶች ጥቃትን የተቃወሙ ሰልፈኞች ፊታቸውን በሸፈኑ ሰዎች የያዟቸው ምስሎች መቀደዱ ነው የተገለጸው።

በኢስታንቡል ደግሞ ፖሊስ ሰልፍ የወጡ ሴቶች ላይ አስለቃሽ ጋዝ መተኮሱም በዘገባው ተጠቅሷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም