የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር ተጠናቀቀ

75

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30/2012 ( ኢዜአ) የሐበሻ ሲሚንቶ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር ትናንት በተካሄዱ ጨዋታዎች ፍጻሜውን አግኝቷል። 

ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ ጌታዘሩ ስፖርት ክለብና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ናቸው።

ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል።

የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ጌታዘሩ ስፖርት ክለብን በአምስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ከ 2 ለ 0 መመራት ተነስቶ ነው ጨዋታውን ማሸነፍ የቻለው።

በውድድሩ መመሪያ መሰረት አንድ የቮሊቦል ጨዋታ 3 ለ 2 ከተጠናቀቀ አሸናፊው ቡድን ሁለት ነጥብ፣ ተሸናፊው ቡድን አንድ ነጥብ ያገኛሉ።

በዚሁ መሰረት ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ሁለት፣ ጌታዘሩ ስፖርት ክለብ አንድ ነጥብ አግኝተዋል።

በሌላ ጨዋታ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አዲሱን የሊጉን ተሳታፊ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

በዚሁ መሰረት አራት ክለቦች እየተሳተፉበት የሚገኘው የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር ተጠናቋል።

ተተኪ ተጫዋቾችን አለማፍራትና ለሴቶች ቮሊቦል ስፖርት ተገቢው ትኩረት አለመሰጠቱ ለክለቦች ቁጥር ማነስ በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ ነው።

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ክለብ አቋቁሞ ወደ ውድድር ቢገባም አንጋፋው የኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች ባለፈው ዓመት ክለቡን አፍርሷል።

ለሴቶች ቮሊቦል የሚፈለገውን ትኩረት መስጠትና የታዳጊ ወጣቶች የቮሊቦል ፕሮጀክቶችን ማጠናከር ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻና 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትናንትናና ከትናንት በስቲያ በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ተካሄደዋል።

ትናንት መቐለ ላይ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ቡታጅራ ከተማን 54 ለ 20 በሆነ ሰፊ ልዩነት ያሸነፈ ሲሆን የመጀመሪያውን ዙር ውድድርም በመሪነት አጠናቋል።

ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን 35 ለ 28 አሸንፏል።

ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ተካሄደዋል።

ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከምባታ ዱራሜን 47 ለ 31 ሲያሸንፍ መከላከያ ፌዴራል ፖሊስን 36 ለ 33 አሸንፏል።

የፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር ውድድር ከሁለት ሳምንት እረፍት በኋላ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተመሳሳይ 16 ነጥብ እርስ በእርስ ሲገናኙ ባሸነፈ በሚለው ህግ በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።

መከላከያ በ14 ነጥብ ሶስተኛ፣ የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ12 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

አዲሱ የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ሚዛን አማን ከተማ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 10ኛ ደረጃ ይዟል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ትናንት ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል።

በሴቶች ወልቂጤ ላይ ሐዋሳ ከተማ ወልቂጤ ከተማን 66 ለ 12 ሲያሸንፍ በወንዶች ደግሞ ወልቂጤ ከተማ ሐዋሳ ከተማን 48 ለ 45 አሸንፏል።

በተለያዩ ምክንያቶች ያልተካሄዱ የአራተኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች በሴቶች መጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም በወንዶች መጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚካሄዱ የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም