የድሬዳዋ ሴቶች ለሰላም ዘብ በመቆም ለፍትሃዊ ተጠቃሚነታችን እንሰራለን አሉ

124

ድሬዳዋ ኢዜአ የካቲት 29 ቀን 2012  ሀገራዊ ሰላም በማስፈን በሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ እኩል ተሳታፊነታችንና ተጠቃሚነታችን ለማረጋገጥ ኃላፊነታችነን በብቃት እንወጣለን ሲሉ የድሬዳዋ ሴቶች ገለፁ ። 
በሀገር ደረጃ ለ44ኛው ጊዜ እየተከበረ ያለው አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ዛሬ በድሬዳዋ ከተማ የህብረተሰቡንና የሴቶች ግንዛቤ በሚያጎለብቱ ተግባራት በድምቀት ተከብሯል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ከሪማ አሊ በዓሉ ዛሬ በፓናል ውይይት በተከበረበት ወቅት እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት የሴቶችን ማህበራዊ፣ የምጣኔ ሃብትና የፖለቲካ ተሣትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ለውጦች ቢመጡም አሁንም ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡

በአስተዳደሩ በገጠርና በከተማ ቀበሌዎችና ጽህፈትቤቶች በአመራርነት ደረጃ የሚገኙ ሴቶች ቁጥር መጨመሩ ሴቶች በሁሉም መስክ ተጠቃሚነታቸው እንዲጎለብት እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እነዚህን ለማጠናከርና አሁንም በወጣቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ያልተሻገርናቸውን ጥቃቶችን በተባበረ መንገድ ለመከላከል በህብረት ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

ሰፊ አደረጃጀቶች ተፈጥረው አጥፊዎች በህግ እንዲጠየቁና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ የተጀመረውን ሥራ ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልፀዋል ።

ሴቶች በሁሉም መስክ ተሳታፊነታቸውና ተጠቃሚነታቸው ተረጋግጦ በሀገር አቀፍ  የብልጽግና ጉዞ ላይ ስኬታማ እንዲሆኑ ከቤተሰብ ጀምሮ እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል ።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር ለማድረስ ሴቶች እንደቀድሞ ተሣትፎአቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በዓሉን ካከበሩ ሴቶች መካከል ወይዘሮራዚያ ሣሊህ በሰጡት አስተያየት በገጠር ቀበሌዎች ሴቶችን ከማጀት በማውጣት በትምህርት ፣በልማት፣ በጤናው ዘርፍ ተጠቃሚ የማድረጉ ተግባር ውጤት እያመጣ ይገኛል ብለዋል ።

ውጤቱን ለማጠናከር መሰረታዊ ጉዳይ የሀገራችንን በተለይ የድሬዳዋ አንጻራዊ ሰላምን በአስተማማኝ መንገድ ዘላቂ ማድረግ ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ከበቡሽ ይልማ ናቸው፡፡

ወ/ሮ አይንአዲስ ሉሉ በበኩላቸው በከተማው አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን እኛ እናቶች ልጆቻችንን ከቤት ጀምሮ እስከ ውጪ ያለውን እንቅስቃሴያቸውን በተገቢው መንገድ መቆጣጠር ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ተሣትፎም ሆነ ተጠቃሚነት እውን የሚሆነው ሰላም ሲኖር በመሆኑ እናቶች እንደቀድሞ ፍቅርና አንድነታችንን ጠብቀን ለድሬዳዋ ዘላቂ ሰላም ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን ሲሉ የበዓሉ ታዳሚዎች ተናግረዋል ።

‹‹የሴቶች ደህንነትና መብት መከበር ለሰላማችንና ለህልውናችን መሰረት ነው›› በሚል መሪ ሃሳብ በተከበረው በዓል ላይ የድሬዳዋ ከተማና የገጠር ሴቶች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም