አገር በቀል የተፈጥሮ ደን ጠብቆ ለማቆየት ዘር የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ ነው

261

መቐለ (ኢዜአ) የካቲት 29/2012 የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ በክልሉ የሚገኙ የአገር በቀል የተፈጥሮ ደን ሀብቶችን ጠብቆ ከጥፋት ለመታደግ ዘራቸውን የማሰባሰብና የማራባት ስራ እያከናወነ መሆኑን ገለፀ።

በቢሮው የደን ልማት አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ሙኡዝ ሃይሉ ለኢዜአ እንደገለጹት ቢሮው በክልሉ የሚገኙ 21 ዓይነት አገር በቀል የተፈጥሮ የደን ዝርያዎችን አሰባስቦ በችግኝ ጣብያ የማፍላት ስራ እየተከናወነ ነው።

ክልሉ ለአገር በቀል ደኖችን ትኩረት በመስጠት 36 ሚሊዮን ችግር በማፍላት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ችግኙ በሚቀጥለው ክረምት በ450 ሺህ ሄክታር መሬት በሚሸፍን የደን ሀብት ላይ ተጨማሪ የአገር በቀል ችግኝ ተከላ ይካሄድበታል ብለዋል።

አገር በቀል ችግኝ የሚተከልባቸው የደን ክልሎች ዴስአ፣ሕጉም ቡርዳ የደን ክልሎችና ቃፍታ ሸራሮ ብሄራዊ ፓርክ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

አገር በቀል ዘር የማሰባሰብ ስራው እየተከናወነ ያለው ከደን ክልሎችና ከገደማትና የእምነት ተቋማት ስፍራዎች፣ እንዲሁም በህብረተሰቡ ተተክለው ከለሙ  ቦታዎች እንደሆነ ገልጸዋል።

ከሚሰበሰበው የተፈጥሮ ደን ዘር መካከል የአበሻ ጥድ፣ወይራ፣ዋንዛና ቆንጥር ጨምሮ ሞሞና፣ዝሓይና ሑመር የተባሉ የደን ዝርያዎች ይገኙበታል ።

በተለይ በክልሉ በመጥፋት አደጋ ላይ የሚገኙ  የተፈጥሮ የደን ዝሪያዎች የኮሶ ዛፍ፣ቀርካሃ ፣ግራርና  ሑመር  መልሶ ለማገገም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የአገር በቀል ዘር የማሰባሰብ ዋና አላማው ዝርያቸው  እንዳይጠፋ ከመጠበቅ ባለፈ የአካባቢው ስነ ምህዳር ለመጠበቅ እንደሆነም አቶ ሙዑዝ ተናግረዋል።

የትግራይ  ደን ዘር ማእከል  አስተባባሪ አቶ አሊ ሓዱሽ በበኩላቸው በዚህ አመት ለዘር የሚሆን 120 ኩንታል የአገር በቀል ዛፍ ፍሬ  ለማሰባሰብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

 ዘሩ የማሰባሰብ ስራው የሚካሄደው በ13 ማህበራት አማካኝነት መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም መንግስት 3 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን ጠቅሰዋል።

ዘር በማሰባሰብ ከተሰማሩ ማህበራት ውስጥ በክልተ አውለዓሎ  ወረዳ በአብርሃ ወአፅብሃ ቀበሌ ገበሬ ማህበር  "መሰረት" የተሰኘ ማህበር አንዱ ነው።

የማህበሩ አባል አቶ ኪሮስ አብርሃ እንደገለጹት ማህበሩ በዚህ አመት ሰባት ኩንታል ''የሞሞና ዛፍ''ዘር  አሰባስቦ ለማእከሉ ለማስረከብ ውል ፈፅሞ እየሰራ ነው ።

ማህበሩ ለአንድ ኪሎ ግራም የ''ሞሞና'' ዘር በ95 ብር ሂሳብ ለማስረከብ ግዴታ መግባቱን ተናግረዋል።

 የአገር በቀል ዛፎችን ዘር መሰብሰብ የዘር አይነቶች በመለየት በጥናትና ምርምር የታገዘ የደን ተካላ እንዲካሄድ ያግዛል  ያሉት ደግሞ በትግራይ ክልል እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት የተፈጥሮ ሃብት ምርምር አስተባባሪና የተፈጥሮ ደን ተመራማሪ አቶ ክንፈ መዝገበ ናቸው።

በክልሉ የአገር በቀል ዛፎች ዘር የማሰባሰብ ስራ የተጀመረው ባለፈው አመት ሲሆን የክልሉ የደን ሽፋን ከ13 በመቶ ወደ 18 ከመቶ ከፍ ማለቱን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም