የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራው ዘመናዊነት እንዲላበስ የተደረገ ነው

79

ማይጨው /ኢዜአ/የካቲት 29/2012ዓም በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን የሚካሔደው የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ የሚታይ ፣ የሚዳሰስና ተጠያቂነት ሲነሳ ግልፀ መረጃ ማቅረብ በሚያስችል መልኩ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ አስታወቀ ።

የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ አስተባባሪ  አቶ ፍሳሃ ገብረኪዳን ለኢዜአ እንደተናገሩት የዘንድሮው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ስራ ካለፈው የካቲት 3 ቀን 2012 ዓም ጀምሮ በተጠናከረ መልኩ እየተካሔደ ነው ።

ከአሁን በፊት ይካሄድ የነበረው የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ መሬት ተለክቶና በካርታ ተደግፎ ባለመከናወኑ የተከናወኑ ስራዎች የሚመዘኑት በግምት ነበር ብለዋል ።

ግምታዊ ምዘናው ለተዛቡ ሪፖርቶች ምክንያት ሆነው መቆየታቸውንም አስተባባሪው ተናግረዋል ።

ዘንድሮ ግን በዞኑ በ184 ተፋሰሶች  በ5 ሺህ 800 ሔክታር መሬት ላይ በመካሄድ ላይ ያለው የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ  በጂፒኤስ ካርታ  የተሰራለት በመሆኑ የተሰራውንና ያልተሰራውን በግልፅ ለመለየት ያስችላል ።

ይህም በምን ያህል ስፋትና ምን አይነት የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ እንደሚከናወን በግልጽ የሚያሳይ በመሆኑ ግምታዊ ሪፖርቶችን ሙሉ በሙሉ እንደሚያስቀር ተናግረዋል።

ከአሁን በፊት የሚታቀደውና መሬት ላይ የሚሰራው ስራ ልዩነት ነበረው የሚሉት አስተባባሪው አሁን ግን ካርታውን መሰረት በማድረግ ቆጥሮ የመስጠትናና ቆጥሮ የመረከብ ስርአት መዘርጋቱን ገልጸዋል።

በዘመቻው በየቀኑ 170 ሺህ የዞኑ ህዝብ እየተሳተፈ ነው ተብሏል ።

ተዳፋት መሬት ላይ የሚሰራው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የጎርፍ ውሃ በመግታትና ውሃን በማቆር ወራጅ ወንዞችና ምንጮች እንዲጎለብቱ አድርጓል ያሉት ደግሞ በእምባ አላጀ ወረዳ የዓይባ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር ግርማይ ረዳኢ ናቸው።

በተጨማሪም የአካበቢው ለምነትን በመመለስ  ለግጦሽ የሚሆን ሳር በአቅራቢያቸው ለማግኘት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።።

የመሬት ለምነት እየጨመረ በመምጣቱ   ከአንድ ጥማድ መሬት የሚያገኙትን የስንዴ ምርት በእጥፍ መጨመሩን አስረድተዋል ።

ከዚህ በፊት የአርሶ አደሩ ግንዛቤ አነስተኛ ስለነበር ደኑን እየመነጠሩ ለማገዶና ለእርሻ አገልግሎት ያውሉት እንደነበር የገለጹት ደግሞ የራያ ዓዘቦ ወረዳ የሐወልቲ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር ልኡል ሓዱሽ  ናቸው።

አሁን በአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ የተሸፈነው መሬትና አካባቢ ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነፃ ተደርጎ በመከለሉ ለምነት ቀንሶ የነበረው የእርሻ መሬታችን ማገገም ጀምሯል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም