ስኬታማና ተጽዕኖ ፈጣሪና ሴቶች ሌሎችን ለማፍራት ድጋፍና እገዛ ማድርግ እንዳለባቸው ተጠቆመ

117

የካቲት 29/2012 (ኢዜአ) በተለያዩ የሙያ መስኮች ስኬታማና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ሌሎች የእነርሱን አርአያ እንዲከተሉ እገዛና ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሴት የበረራ ባለሙያዎች ገለጹ።

በፖለቲካ፣ በቢዝነስ፣ በስራ ፈጠራና በተለያዩ የሙያ መስኮች በዓለም ስኬታማ የሚባሉ ሴቶች ቁጥር በእጂጉ እየተበራከቱ መምጣታቸው ይነገራል።

በኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዙ የስራ መስኮች ላይ የሴቶች ተሳትፎና ሚና እየጎላ የመጣ ሲሆን ስኬታቸውም በዚያው ልክ እያሻቀበ ይገኛል።

ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ ትናንት ማምሻውን በሴቶች ብቻ የሚመራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቡድን ወደ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ አቅንቷል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ፓይለቶች እንዳሉት ማንኛውም ሰው ስኬታማ ለመሆን የራሱ ጥረቶች ግድ ቢሉትም የቤተሰብ፣ የማህበረሰብና በስኬት ጎዳና ላይ ያሉ ግለሰቦች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በአሁኑ ጊዜ በርካታ ጠንካራ ሴቶች በለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በስራ እና በትምህርት ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ውጥናቸው ዳር እንድደርስ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ምክትል አብራሪ የሆነችው ሰላማዊት አለማየው ''ስኬት በአንድ ጊዜ የሚመጣ ጉዳይ ሳይሆን በተለያዩ ውጣውረዶች ወስጥ በማለፍ የሚገኝ መሆኑን ከራሷ ተሞክሮ በመነሳት ገልፃለች

እርሷ ለደረሰችበት ስኬት የራሷ ጥረትና ትጋት እንዳለ ሆኖ የቤተሰብና የሌሎች ሰዎች እገዛ ደግሞ ይበልጥ ለስኬቷ እንዳገዛት ትናገራለች።

በመሆኑም በስኬት መንገድ ላይ ያሉ፣ ስመጥር እና ተጽእኖ ፈጣሪ ሴቶች ለሌሎች ሴቶች የስኬት መንገድ አሻራ ቢኖራቸው ብዙዎችን ወደ ስኬት ማማ ማምጣት እንደሚቻልም ትናገራለች።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ረዳት አብራሪ ህሊና በየነም በዚሁ ሃሳብ ትስማማለች።

በገጠሪቷ የኢትዮጵያ የሚኖሩ በርካታ ሴቶች ነገሮች ባልተመቻቹበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለስኬት ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል ያለችው ህሊና የሌሎች ድጋፍ ቢደረግላቸው ስኬታማ እንደሚሆኑ ትናገራለች።

በመሆኑም በተለያዩ የስራ መስኮችም ይሁን በትምህርት ላይ የሚገኙ ሴቶች የሁላችንም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብላለች።

ሌላኛዋ ረዳት አብራሪ ፍሬህይወት በላይ በበኩሏ በማህበረሰቡ ዘንድ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሴቶች ያላቸውን አቅም ተጠቅመው እንዳይሰሩ ጫናዎች መኖራቸውን ትናገራለች።

የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ የወንዶች አጋርነት፣ የቤተሰብና የማህበረሰብ ድጋፍ በይበልጥ ደግሞ የስኬታማ ሴቶች ድጋፍ ያስፈልጋል ብላለች።

ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን (ማርች8) ዛሬ በመላው ዓለም በተለያዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም