የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት አዋጅ ተግባራዊነት ላይ ጥንቃቄ ያሻል

86

አዲስ አበባ የካቲት 28/2012 (ኢዜአ) የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ወደ ስራ ለመተርጎም ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ። 

ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽ መብት ጋር ተያይዞ አከራካሪ ሃሳቦች ሲነሱብት የቆየው የጥላቻ ንግግርና ሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ከሳምንታት በፊት ፀድቋል።

በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግለሰቦችና ቡድኖችን፣ ሃይማኖትን፣ ብሄርን፣ ዘርን፣ ጾታና አካል ጉዳተኝነትን መሰረት ያደረገ የጥላቻና ሀሳተኛ መረጃ ጉዳይ ሕጋዊ መፍትሔ ካልተበጀለት ለአገር ሠላምና ደህንነት ከፍተኛ ስጋት መሆኑም ለአዋጁ መውጣት አስፈላጊነት እንደ አመክንዮ ቀርቧል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሙያዎችም አዋጁ ኢትዮጵያ ለገጠማት ችግር አስፈላጊ ቢሆንም ትግበራው ግን ጥንቃቄ እንደሚያሻው አልሸሸጉም።

የሕግ ባለሙያው አቶ ወንድሙ ኢብሳ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ልሂቃን ከ1960ዎቹ ጀምሮ ለታዋቂነትና ዝና እንጂ አገር ለማበልጽግ የሚጫወቱት ሚና እንደሌለ ይገልጻሉ።

በተለያዩ ማንነቶችን ሽፋን ከመንግስት ባለስልጣናት እስከ ተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ጠብ ጫሪና ስድብ አከል አካሄዶች እንደተበራከቱ ገልጸው፤ አዋጁ 'ለአፍ ለከት እንዲኖረው ይጠቅማል" ብለዋል።

በዓለም ልሂቃን ላይ በተደረገ ጥናት የጥላቻና ሀሰተኛ መረጃዎች መታገድ እንዳለባችው መረጋገጡን ያነሱት አቶ ወንድሙ፤ በኢትዮጵያ መውጣቱም ተገቢ እንደሆነ ያምናሉ።

የአቶ ወንድሙን ሃሳብ የሚጋሩት ፖለቲከኛው ዶክተር ቴዎድሮስ ኃይለማርያምም የዘመናዊ ኢትዮጵያ ፖለቲካ በጥላቻ ባሕል ላይ የተመሰረተና አንዱ ሌላውን በማጥላላት ላይ የቆመ እንደሆነ ይናገራሉ።

ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አንጻራዊ እንደሆነ ገልጸው፤ ከመደበኛ እስከ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት ጦርነት ቀስቃሽ አካላት እንዳሉም ያነሳሉ።

በመሆኑም በአገርና በማኅበረሰብ ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመከላከል በአዋጁ መውጣት ተገቢነት ያምናሉ።

አስተያየት ሰጪዎቹ በአዋጁ አስፈላጊነት ቢያምኑም ትግበራው ላይ ግን የከዚህ ቀደሙን የፀረ-ሽብር አዋጅ አወጣጥና አተገባበር በመጥቀስ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

መንግስትን የሚመራው ገዥ ፓርቲ ሕጉን በቅንነት እንጂ ደጋፊዎቹን ለመጥቀም፣ የሚቃወሙትን ለማጥቃት ማዋል እንደሌለበትም አሳስበዋል።

መንግስት ብቻም ሳይሆን ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማኅበራት በሕጉ ትግበራ ሃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በተለይም ሕዝቡ መብትና ነጻነቱ እንዳይነካ በአዋጁ ትግበራ ብቻ ሳይሆን ሕጉን ለሚተላለፉትም እምቢተኝነቱን ማሰማት እንዳለበትም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም