በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከ15ሺህ በላይ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የውሃ መስመር ዝርጋታ ተከናወነ

115
አሮሚያ ልዩ ዞን 21/ 2010 በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከ15ሺህ በላይ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የውሃ መስመር ዝርጋታ ማከናወኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ገለጸ። ባለስልጣኑ 31 የመጠጥ ውሃ መስመሮችን በልዩ ዞኑ በሚገኙ አራት ወረዳዎች መዘርጋቱን ጠቅሶ ለስራውም 79 ሺህ ብር ወጭ መደረጉን ጠቁሟል። 15ሺ552 አባወራዎችና እማወራዎችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ የተባለላቸው እነዚህ የውሃ ቦኖዎች በልዩ ዞኑ ውስጥ በመሪኖ፣ በአቃቂ፣ በኤቹና በሰበታ ዙሪያ ደወረ ጉዱ ወረዳዎች የተገነቡ ናቸው። እነዚህ ወረዳዎች ለረጅም ጊዜ ከፍተኛ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር የነበረባቸው ሲሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ክልሉን ለማገዝ በሚል የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ስራውን ማከናወኑን ባለሰልጣኑ ገልጿል። ባለስልጣኑ አገልግሎት መስጠት የጀመሩትን እነዚህን የንጹህ መጥጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለጋዜጠኞች አስጎብኝቷል። የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን የስራ ሂደት መሪ አቶ እስጠፋኖስ ብስራት እንደገለጹት፤ ባለሰልጣኑ የነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ለማሳደግ በኦሮሚያ ልዩ ዞን በሚገኙ አራት ወረዳዎች 31 የውሃ ቦኖዎችን ግንባታ አጠናቆ ለነዋሪዎች አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል። የመሪኖ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሽቱ አወል በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር እንደነበረባቸው አስታውሰው የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ባደረገው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግሩ መቃለሉንና የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍለጋ ያጠፉት የነበረውን ጊዜና ጉልበት እንቀነሰላቸው አክለዋል። የአቃቂ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ ልባቡሽ ረታ በበኩላቸው አካባቢያቸው የንጹህ መጠጥ ውሃ ሳያገኝ ከአካባቢው ተቆፍሮ የሚወጣው የከርሰ ምድር ውሃ ለአዲሰ አበባና ሌሎቸ አካባቢዎች እየተዳረሰ እነርሱ ለረጅም ጊዜ ሲቸገሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። አሁን ላይ ችግሩ በተወሰነ መጠን የተቃለለ ቢሆንም ለእንስሳት መጠጥ አገልግሎት የሚውል ውሃ ባለመኖሩ መቸገራቸውን ጠቁመው መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። የስራ ሂደት መሪው አቶ አስጢፋኖሰ በበኩላቸው የተነሳው ችግር ትክክል መሆኑንና ለእንስሳት መጠጥ አገልግሎት የሚውል የውሃ ፕሮጀክት ለመገንባታ ጥናት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል። በቀጣይም ባለስልጠኑ በፊንፊኔ ዙሪያ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ያለውን የውሃ ችግር ለመቅረፍ  ከፍተኛ በጀት መድቦ ግንባታዎችን ለማካሄድ ማቀዱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም