የደሴ መምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ባለማግኘታቸው መቸገራቸውን ገለፁ

77
ደሴ ሰኔ 21/2010 መንግሥት ለመምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጥ ቢፈቅድም ተግባራዊ ባለመሆኑ መቸገራቸውን በደሴ ከተማ አስተዳደር የሚኖሩ መምህራን ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡ በአካለወልድ ክፍተኛ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ፍቅር አበበ ለኢዜአ እንደገለፁት የመምህራንን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ መንግሥት የቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጥ ቢፈቀድም በከተማው እስካሁን ተግባራዊ ሊደረግልን አልቻለም። በዚህም የተነሳ ከግለሰቦች ለተከራዩት ቤት የደሞዛቸውን ግማሽ እንደሚከፍሉ ጠቁመው፤ ይህም በኑሯቸው ተጽእኖ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ በተለይ በየጊዜው የሚጨምረው የኑሮ ውድነት የሚያሳድረው ስነ ልቦናዊ ጫና ከፍተኛ በመሆኑ በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረባቸው መምጣቱን አመልክተዋል። የቦታ አቅርቦት ጥያቄያቸው እልባት እንዲያገኝ በመሰረታዊ የመምህራን ማኅበራቸው በኩል ለከተማ አስተዳደሩ ከአንድ ዓመት በፊት ቢያቀርቡም እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸው ቅሬታ እንደፈጠረባቸው አመልክተዋል። በደሴ ቢለን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር መኮነን ታደለ በበኩላቸው ቦታ ለማግኘት ግንባታ ማስጀመሪያ ገንዘብ እንዲያስገቡ በታዘዘው መሰረት ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም /አብቁተ/ 32 ሺህ ተበድረው ማስገባታቸውን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከአበዳሪ ተቋሙ የተበደሩትን ገንዘብ ቦታው ሳይሰጥና ገንዘቡ ስራ ሳይሰራበት በመቆየቱ በየወሩ ለወለድና ለተጨማሪ ወጭ እንደዳረጋቸው ገልፀዋል፡፡ የደሴ ከተማ መምህራን ማኅበር ፀሃፊ አቶ ተፈራ ካሳ የመምህራን ቅሬታ በማንሳት በተደጋጋሚ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ለመነጋገር ቢሞከርም ጥያቄቸው እስካሁን ምላሽ እንዳላገኘ ተናግረዋል፡፡ ችግሩ በወቅቱ ባለመፈታቱ ከአራት ወር በፊት ለክልሉ ከተማ ልማትና ትምህርት ቢሮዎች በቃልና በደብዳቤ አስታውቀው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ "መንግሥት ቃል የገባውን አለመፈጸም የመልካም አስተዳደር ችግር መገለጫ ነው" ብለዋል፡፡ የደሴ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ስራ አስኪያጅ አቶ ሃሰን ሙህዬ የክልሉ መንግሥት በተለየ መንገድ ለመምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው የሚያዘው መመሪያ በዚህ ዓመት መውጣቱን አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ በወጣው መመሪያ መሰረት የመምህራኑን ጥያቄ ማስተናገድ ያልተቻለው በከተማው መጥበብ ምክንያት ወደ መሬት ባንክ የገባ ቦታ ባለመኖሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ አዝዋ ገደል በሚባለው አካባቢ ካሳ ተከፍሎበት የነበረ ቦታ ቢኖርም አርሶ አደሮቹን የማስለቀቅ ስራ ረጅም ጊዜ መውሰዱን ተናግረዋል። የአርሶ አደሮቹ የመብት ጥያቄ ከረጅም ጊዜ ውይይት በኋላ ምላሽ በማግኘቱ በዚህ ዓመት መምህራኑን ጨምሮ በከተማዋ ለተደራጁ 41 የቤት ስራ ማህበራት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የቦታ ሽንሸና ተደርጎ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡ የመምህራንን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ አሰጣጥና የተሰራ ቤት ድልድል በክልሉ መስተዳደር ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 150/2009 መውጣቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም