ወርኅ የካቲት ከኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ጋር የመጣባቱ ምስጢር ምን ይሆን?

241

አየለ ያረጋል ( ኢዜአ)

ወርኅ የካቲት ከኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ጋር የመጣባቱ ምስጢር ለምን ይሆን

አንዳንድ ወራትና ቀናት የአገራትን ዕጣ ፈንታ ይወስናሉ፣ ታሪክ ይቀይራሉ፤ ዘመን ተሻጋሪ አሻራ አሳርፈው ሲያልፉ በትውልድ ይዘከራሉ። 

በኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ውስጥ ከሁለት ቀናት በኋል በሚጠናቀቀው ወርኃ የካቲትን ያክል በየታሪክ ህዳጉ የኢትዮጵን ዕጣፈንታ የወሰነ ወቅት ያለ አይመስልም።

ወርኃ የካቲት በመካከለኛው ዘመን ዝነኛውን ንጉስ አጼ ሠርፀድንግልን፣ "የዘመናዊት ኢትዮጵያ ጠንሳሽ ናቸው" የሚባሉትን አጼ ቴዎድሮስንና ንግስት ዘውዲቱን አንግሷል።

ከጦረኞቹም ግራኝ አህመድን፣ እቴጌ ጣይቱን፣ ንጉስ ወልደጊዮርጊስን፣ ራስ ደስታ ዳምጠውን፣ ራስ አሉላ እንግዳንና ሌሎች ብሔራዊ የጦር ጀግኖችን አሳርፏል።

በሌላ በኩል በኪነ ጥበብ መስክ ደግሞ ወርኅ የካቲትን ያህል የሞት ዶፍ የወረደበት ወቅት እንደሌለ ብዙዎቹ ይስማማሉ።

ለአብነትም ሞገደኛው ብዕረኛ አቤ ጉበኛ እረፍት የካቲት 2፣ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር የካቲት 12፣ ጸጋዬ ገብረመድህን የካረቲት 18፣ ማሞ ውድነህ የካቲት 23፣ እንዲሁም ተወዳጁ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ እንደወጣ የቀረው የካቲት 24 ነበር።

በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ደጋማ ክርስቲያኖች ከሙስልም ሱልጣኔቶች ጋር ተደጋጋሚ የእርስ በርስ ጦርነት ያካሄዱበት፣ በ1929 ዓ.ም 30 ሺህ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በጅምላ በአካፋና በዶማ በግፍ የተጨፈጨፉትም በወርኃ የካቲት ነው።

የ1928ቱ የጣሊያን ወረራ በሽሬ፣ በተንቤን እና በአምባራዶም የጦር ሜዳዎች የተከለከለ መርዝ በኢትዮጵያዊያን ላይ ተርከፍክፎ እንዲቃጠሉ መደረጉም የታሪክ ድርሳናት እማኝ ናቸው። 

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በወርኃ የካቲት ለጥቁር ህዝቦች ቀንዲል የሆነውን የጣሊያን ወረራን በአድዋ፣ የግብጽን ወረራ በጉራ፣ የሶማሊያ ጦርነትን በካራማራ ድል የተቀዳጀችበት ነው።

በወርኃ የካቲት ጀምበር ገበሬዎች በአጼ ኃይለሥላሴ ላይ አምጸዋል።

እንዲሁም መምህራንን፣ ተማሪዎችን፣ አሽከርካሪዎችን፣ የመንግስት ሠራተኞችን፣ የእስልምና ሐይማኖት ተከታዮችንና ወታደሮችን ለተቃውሞ ወደ አደባባይ አስወጥቷል- ሕዝባዊ አብዮትም ቀስቅሷል።

እናም ወርሃ የካቲት የአመጽም፣ የድልና የሃዘንም ታሪካዊ ገጾች ባለቤት የመሆኑ ምስጠር ለምን ይሆን?

የታሪክ ምሁሩ ዶክተር ቴዎድሮስ ሃይለማርያም ወርሃ የካቲት ገበሬው የሚያርፍበት፣ወንዞች ደርቀው ሰው የሚገናኝበት በመሆኑ እንዲሁም የጾም ወቅት መሆኑ የውጭ ጠላቶች አስልተው እንደሚመጡ ጠቅሰው፤ ለአብነትም በሰንበትና በፆም ወቅት የተደረገውን አድዋን ያነሳሉ።

በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪው ዶክተር አልማው ክፍሌ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ገበሬ የሆነባት ኢትዮጵያ ካሏት 13 ወራት መካከል ወርኃ የካቲት ለገበሬው ጥጋብ፣ ለመንግስታት ደግሞ የግብር መሰብሰቢያ ወር ነው ይላሉ።

ወርኃ የካቲት ምርት ተሰብስቦ ጎተራ የሚገባበት፣ ሰርግ የሚሰረግበት፣ ሽፍታ የሚበረታበት ወቅት እንደሆነ የገለጹት ተመራማሪው፤ 'በግብር ገብር! አልገብርም!' በሚል ግብግብ የገበሬ አመጽ የታየበት ወር መሆኑን ያወሳሉ። 

በሌላ በኩል ወቅቱ ተማሪዎች ከአንደኛው መንፈቅ ዓመት ወደ ሁለተኛው የሚሸጋገሩበት በመሆኑ ተማሪዎችም ለንቅናቄ ያነሳሳ ወቅት መሆኑን በ1960ዎቹ የተደረገውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመሬት ለአራሹ፣ የዴሞክራሲ፣ የኃይማኖትና የብሔር ጥያቄዎችን ያነሱበትና አብዮት የቀሰቀሱበት እንደነበር ዶክተር አልማው ይናገራሉ።

'የካቲት በርካታ የምንኮራባቸው ሰዎች የተወለዱበት፣ ያጣንበትም ወር ነው' የሚለው በባህል፣ ቱሪዝምና ታሪክ ዙሪያ የሚሰራው ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ነው።

የካቲትና የኢትዮጵያ ታሪክ ግንኙነት ድል የተገኘበት፣ መጥፎ ጠባሳዎችንም ያተምንበት ወቅት በመሆኑ ወርኅ የካቲትን በግጥምጥሞሽ የተሞላ፤ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ጋር ተነጥሎ የሚታይ አለመሆኑን ይገልጻል።

ከዚህ በፊት በጉዳዩ ላይ በሰጠን ምላሽ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የማንነት፣ የሀዘን ሁነቶችን ማስተናገዱን ገልጾ፣ የወርሃ የካቲት ሁነቶች ተጻራሪ ታሪኮች እንደሆኑ የካቲት 12 እና የካቲት 23ን ለአብነት ይጠቅሳል።

ከኢትዮጵያ አልፈው እንደ አድዋ ያሉ ለጥቁር ህዝቦች ትግል አብነት የሆኑ ታሪኮች የተፈጸሙበት፣ አብዮት የተካሄደበት የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የተወሰነባቸው ክስተቶችን ያስተናገደ ወር መሆኑን ያነሳል።

ኢትዮጵያ በየካቲት ወር ባሳለፈቻቸው ታሪኮች ልትማር፣ ትውልዱም ታሪኩን ሊያውቅ እንደሚገባ ገልጿል።

ወደ ኋላ ታሪክ ሰርተው ባለፉ ሰዎች ላይ ከመነታረክ ዛሬ በየሰከንዱ በሚስተዋለው የዓለም ተለዋዋጭነት ኢትዮጵያዊያን ከዘረኝነትና መከፋፈል ተላቆ አገራችንን ለማሳደግ ከየካቲት ወር ታሪካዊ ክስተቶች መማር ይገባል ነው ያለው።  

ወርሃ የካቲት ከኢትዮጵያ አልፎ በአጠቃላይ የመብትና ነጻነት ትግሎች የተስተናገዱበት ሲሆን በአገረ አሜሪካ ጥቁሮች ለእኩልነትና ነጻነት የታገሉበት ወቅት በመሆኑ የታሪካቸው አካል በማድረግ ያከብሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም