ኢትዮ-ቴሌኮም ለሴት መምህራን ሽልማት አበረከተ

70

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27/2012 (ኢዜአ) የዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን በዓለም ለ109ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ44ኛ ጊዜ በመጪው እሁድ ይከበራል።

ኢትዮ-ቴሌኮም ቀኑን ''ትውልድ በመቅረጽና በማነጽ ጉልህ ሚና ያላቸው በመንግስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚያስተምሩ ሴት መምህራን ላፕቶፕና የስልክ ቀፎዎችን ሸልሟል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ተቋሙ ማህበራዊ ኃላፊነቶችን ለመወጣት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

በተለይ በትምህርት ዘርፍ ሴቶች የበኩላቸውን እንዲወጡ ተቋሙ ከምን ጊዜውም በላይ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዛሬው እለትም ሴት መምህራን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ መረጃና እውቀት አግኝተው ብቁ ዜጋ ማፍራት እንዲችሉ ሽልማት መስጠቱን ተናግረዋል።

በመላው አገሪቱ በ3 ሺህ 350 የመንግስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ20 ሺህ በላይ ሴት መምህራን እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በዛሬው እለትም ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች አርአያ ናቸው የተባሉ 2 ሺህ 169 መምህራን መካከል በእጣ ለተለዩት 50 ሴት መምህራን የላፕቶፕ እንዲሁም ለ200 መምህራን ዘመናዊ የስልክ ቀፎዎች ተሸልመዋል።

በተጨማሪም ለ2 ሴት መምህራን ከየካቲት 29 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ወራት የሚቆይ በየወሩ የ1 ጊጋ ባይት ኢንተርኔት፣ 200 ደቂቃ የአገር ውስጥ ጥሪና 200 የአገር ውስጥ አጭር የጽሁፍ መልዕክት በስጦታ ተፈቅዶላቸዋል።

በአጠቃላይ በተቋሙ የተደረገው ድጋፍ በገንዘብ ሲሰላ 18 ሚሊዮን ብር ይገመታል።

በእለቱ የተገኙ ሴት መምህራን ተቋሙ በስራቸው ምስጉንና አርአያ ለሆኑ ሴት መምህራን በተነሳሽነት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።

ምሳሌ የሚሆኑ ሴቶች በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆኑ መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም በ2012 ዓ.ም 16 ሚሊዮን ብር በመመደብ በአገሪቱ ባሉ 45 ዩኒቨርሲቲዎች ለሚማሩና እገዛ ለሚያስፈልጋቸው 4 ሺህ ተማሪዎች የኪስ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተመልክቷል።

በተጨማሪም 100 ለሚሆኑ ሴቶች የፋሽን ዲዛይን ትምህርት እንዲማሩ ድጋፍ አድርጓል።

ኩባንያው በትምህርት፣ በጤናና መሰል ተግባራት ማህበራዊ አስተዋዕጾውን እየተወጣ እንደሆነም በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም