የሰላም ሚኒስቴርና ጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎውሺፕ ለምርጫው ሰላማዊነት በጋራ ሊሰሩ ነው

89

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27/2012 (ኢዜአ)  የሰላም ሚኒስቴር እና ጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎውሺፕ ለመጭው ብሄራዊ ምርጫ ሰላማዊነት በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት አደረጉ።

የሁለትዮሽ ስምምነቱን የፈረሙት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባውና የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎውሺፕ ኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ፓስተር ዳንኤል ገብረሥላሴ ናቸው።

ስምምነቱ በክልሎች ለሚገኙ የሚሊሺያና የጸጥታ አካላት በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅትና በድህረ ምርጫ ስልጠና ለመስጠት እንደሚያስችል ተመልክቷል።

በተለይ በቅርበት ወደ ህብረተሰቡ የሚደርሱ የሚሊሻ አባላትን በማሰልጠን በምርጫ ጊዜ የሚከሰቱ ችግሮችን እንዴት መፈታት እንዳለባቸውና ምርጫው ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ማድረግ ነው።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ፍሬዓለም በዚሁ ወቅት እንዳሉት በ2012 ዓ.ም መጨረሻ የሚካሄደው ብሄራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ሃይሉ የማይተካ ሚና አለው።

የተደረገው ስምምነትም የሰላም ሚኒስቴር፣ የጸጥታና የፖሊስ አባላት፣ የደህንነት አካላትና ሌሎችም ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን አስቀድመው እንዲሰሩ ያግዛል።

የጸጥታ አካላቱ የሕዝብ ተቋማት እንደመሆናቸው ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎውሺፕ ኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ፓስተር ዳንኤል በበኩላቸው ስምምነቱ ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆንና ህብረተሰቡ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንዲያካሂድ ያግዛል ብለዋል።

በተለይ በጸጥታና ሰላም ላይ ጉልህ ሚና ያላቸውን ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሆኑ አካላትን በሰላምና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ስልጠና ይሰጣል።

ለዚህም 27 ሚሊዮን ብር እንደተመደበ ገልጸው፤ በምርጫ ሂደት የሚፈጠሩ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል በቂ ስልጠና ይሰጣል ነው ያሉት።

በስልጠናው በመላ አገሪቱ ከ600 ሺህ በላይ ለህብረተሰቡ በቅርብ የሚደርሱ የሚሊሻ አባላትም እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም