የወልድያ ዩኒቨርስቲ ሰራተኞችና ተማሪዎች 343 ሺህ 250 ብር ለተፈናቃዮች ድጋፍ አደረጉ

61
ወልድያ ሰኔ 21/2010 የወልድያ ዩኒቨርስቲ ሰራተኞችና ተማሪዎች ያሰባሰቡትን 343 ሺህ 250 ብር ከኦሮሚያ ክልል ለተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ዛሬ ድጋፍ  አደረጉ። በዩኒቨርስቲው ምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ ከ50 በላይ የአመራሮችና የተማሪዎች ተወካዮችን የያዘ ቡድን ሀራና ቆቦ ከተሞች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፉን አበርክቷል። የዩኒቨርሲቲው የተቋማዊ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንትና የቡድኑ መሪ አቶ ይኸነው በላይ በወቅቱ እንደገለፁት ዜጎች ሰርተው በሚኖሩበት ሃገራቸው የደረሰው መፈናቀል የሚያሳዝንና ሊደገም የማይገባው ነው። ወገኖቹ ለደረሰባቸው መፈናቀል ዘላቂ መፍትሄ እስኪሰጣቸው ድረስ ለከፋ ችግር እንዳይዳረጉ በማሰብና ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑን ለማሳየት ድጋፍ ማድረግ ማስፈለጉን ተናግረዋል ። የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ከወር ደመወዛቸው ላይ በመቁረጥና ተማሪዎችም ከቀለባቸው ላይ በመቀነስ የድጋፍ ገንዘቡን ማሰባሰባቸውን ተናግረዋል ። መንግስት ተፈናቃዮችን በዘላቂነት መፍትሄ ለመስጠት በሚያደርገው ጥረት ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል ። ከተፈናቃዮች መካከል አቶ ደሳለኝ ሙላት በሰጡት አስተያየት ተፈናቃዮች ከዚህ ቀደም የተቸገረን በማብላትም ሆነ በማጠጣት ድጋፍ የማድረግ አቅም እንደነበራቸው አስታውሰው አሁን ለደረሰባቸው ችግር ማዘናቸውን ገልፀዋል ። ወጣት አዲሱ ደሳለኝ በበኩሉ በ1977 ዓ.ም በሰፈራ ከሄዱት ወላጆቹ ኦሮምያ ክልል መወለዱን በመግለፅ ቤተሰቡ በደረሰበት መፈናቀል ማዘኑን ተናግሯል ። ተፈናቃዮች ህብረተሰቡ እያደረገላቸው ያለው ድጋፍ ችግራቸውን ለመቋቋም እያገዛቸው መሆኑን በመግለፅ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ምስጋና አቅርቧል ። ተፈናቃዮች ክረምቱን የሚቋቋሙበት መጠለያ ቤት እንዲሰራላቸውና ትምህርታቸውን ያቋረጡ ልጆችም የሚቀጥሉበት ሁኔታ እንዲመቻች የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲፈልግ ጠይቀዋል ። ከኦሮምያ ክልል ቡኖ በደሌና ከቄለም ወለጋ  ከጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ የተፈናቀሉት ወገኖች ቁጥር ከ1ሺህ 700 በላይ እንደሆነ ታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም