የባንክ ኖቶች የኮሮና ቫይረስ ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
የባንክ ኖቶች የኮሮና ቫይረስ ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ ተጠቆመ
65
የካቲት 27/2012(ኢዜአ)የቆሸሹ የባንክ ኖቶች የኮሮና ቫይረስን ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ የአለም ጤና ድርጅት በሰጠው መግለጫ አስጠንቅቋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ሲባል የቆሸሹ የብር ኖቶች አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የአለም ጤና ድርጅት ያሳሰበ ሲሆን ተጠቃሚዎች ብር ከነኩ በኋላ እጃቸውን በአግባቡ መታጠብ እንዳለባቸውም ነው ድርጅቱ ያስገነዘበው፡፡
የብር ኖቶች አደገኛውን ቫይረስ እንደሚያስተላልፉ እስካሁን ሳይንሳዊ የሆነ ማረጋገጫ ባይሰጥም የአለም ጤና ድርጅት ግን የቆሸሹ የብር ኖቶች ንክኪ ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡
የእንግሊዝ ባንክ በበኩሉ የብር ኖቶች ባክቴሪያ እና ቫይረሶችን ሊሸከሙ ይችላሉ በሚል ደንበኞቻቸው ከአጠቃቀም በኋላ እጃቸውን እንዲያጸዱ መክሯል፡፡
በተመሳሳይ ቻይና እና ደቡብ ኮሪያ ከባለፈው ወር ጀምሮ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የባንክ ኖቶችን ከመጠቀም ይልቅ ቴክኖሎጂን ያማከለ ግብይትን የመተግበር እርምጃ ወስደዋል፡፡