ከመንግስት በተደረገልን ድጋፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠቃሚ ሆነናል …. በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ባለሀብቶች

634

ሑመራ ሰኔ 21/2010 በተደረገላቸው ድጋፍ በተሰማሩበት የግብርና ዘርፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠቃሚ መሆን እንደጀመሩ በትግራይ ምዕራባዊ ዞን በግብርና ኢንቨስትመንት የሥራ ዘረፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ተናገሩ።

በዞኑ በ2010 በጀት ዓመት ከ480 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ፈቃድ ወስደው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርቷል።

በዞኑ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በሰሊጥ ማበጠርና መሸጥ ሥራ ላይ የተሰማራው ” የካሊድ ሰርቪስ ፋርመርስ ኃላፍነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት” ተወካይ አቶ አክሊሉ ልዑል እንዳሉት፣ ድርጅታቸው በ2009 ዓ.ም የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዱን ገልጸዋል።

በተሰማሩበት ሥራ ውጤታማ  እንዲሆኑም በመንግስት በኩል መሬት በነጻ እንዲያገኙ ከማድረግ ጀምሮ በከፊል የገንዘብ ብድር የሚያገኙበትና መሳሪያዎችን ከቀረጥ ነጻ የሚያስገቡበት ሁኔታ መመቻቸቱን ተናግረዋል

በተያዘው በጀት ዓመትም መጀመሪያ በ7 ሚሊዮን ብር የመነሻ ካፒታል ወደ ተግባራዊ ሥራ መግባታቸውንና ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ  ከ13 ሺህ 500 ኩንታል በላይ ሰሊጥ አበጥሮ ወደ ውጭ ከላከው ምርት ገቢውን ለማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።

በእዚህም ድርጅቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ካፒታሉ በእጥፍ በማሳደግ 15 ሚሊዮን ብር ለማድረስ መቻሉን አቶ አክሊሉ አስረድተዋል።

አቶ አክሊሉ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ለ14 ሰዎች ቋሚና ለ31 ሰዎች ጊዜያዊ የሥራ እድል ፈጥሯል።

መንግስት በፈጠረላቸው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በሑመራ በእንስሳት እርባታና ማድለብ ሥራ መሰማራታቸውን የገለጹት ሌላው የግል ባለሃብት አቶ ባራኪ በርሄ ናቸው።

ባለሃብቱ በ2010 በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ በ8 ሚሊዮን ብር የመነሻ ካፒታል የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ከክልሉ መንግስት ሰፊ መሬትና ሙያ ድጋፍ በነጻ ማግኘታቸውን የገለጹት አቶ ባራኪ ፣ በእዚህም ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ካፒታላቸውን ወደ 12 ሚሊዮን ብር ማሳደግ እንደቻሉ ጠቅሰዋል፤

እስካሁንም ለአምስት ሰዎች ቋሚ የሥራ እድል መፍጠራቸውን ነው የገለጹት።

የተሰማሩበት የከተማ ግብርና የሥራ ዘርፍ  አዋጪ በመሆኑ፣ ሌሎች ባለሃብቶችም ወደስፍራው በመምጣት በሚፈልጉት የኢንቨስትመንት ሥራ ቢሰማሩ አትራፊ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

በትግራይ ምዕራባዊ ዞን በተያዘው በጀት ዓመት ከ480 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ከዞኑ የኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ፈቃድ ወስደው በተለያዩ የሥራ መስኮች መሰማራታቸውን የገለጹት ደግሞ በጽህፈት ቤቱ የፕሮሞሽን ባለሙያ አቶ አማኑኤል ብርሃነ ናቸው።

እንደባለሙያው ገለጻ፣ ባለሃብቶቹ በኢንዱስትሪ፣ በከተማ ግብርና፣ በኮንስትራክሽን፣ በሆቴልና ቱሪዝም የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ሲሆን በመንግስት በኩልም የተለያዩ ድጋፎች ይደረጉላቸዋል።

የባለሀብቶቹ 480 ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ወደሥራ ሲገቡ ከ27 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚና ጊዚያዊ የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ አመልክተዋል።

የትግራይ ምዕራባዊ ዞን ለግብርና ሥራ ካለው አመችነት የተነሳ በክልሉ መንግስት የልማት ኮሪደር ነው ተብሎ በክልሉ መንግስት የተለያዩ የልማት አውታሮች እየተሟላለት መሆኑ ተመልክቷል።

በእዚህ ምክንያት በ2009 ዓ.ም በግብርና ዘርፍ ብቻ 387 ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ያወጡ ሲሆን፣ የካፒታል መጠናቸውም ከ402 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን አቶ አማኑኤል ገልጸዋል።

በሰቲት-ሑመራ ወረዳ ብቻ በ2010 በጀት ዓመት 100 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 8 የግብርና ፕሮጀክቶች ፈቃድ መውሰዳቸውን የተናገሩት ደግሞ የወረዳው የኢንቨስትመንት መስፋፋት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ደረጀ ደመቀ ናቸው።