በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ ነው - የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ

159
ባህር ዳር ሰኔ 21/2010 ''በባህርዳር ከተማ በመጭው እሑድ የሚደረገውን የድጋፍ ሰልፍ ለማወክ ቦምብ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ'' እየተባለ በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ወሬ ከዕውነት የራቀ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ። የባርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ዳኘው ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ሰልፉ ያለምንም የፀጥታ ችግር ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅም ፖሊስ ከከተማው ወጣቶች ጋር በመተባበር የክትትልና የቁጥጥር ስራ እያከናወነ ይገኛል። ''ሰልፉን ለማወክ በከተማዋ እብድ መስለው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ቦምብ ይዘው በቁጥጥር ስር ዋሉ'' እየተባለ በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ወሬ ከዕውነት የራቀ መሆኑን ተናግረዋል። ''እስካሁንም በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የተገኘ ምንም አይነት የመገናኛ ሬዲዮም ሆነ ቦምብ የለም'' ሲሉ ኮማንደር ዋለልኝ ገልፀዋል። በእኛ በኩል ለሚካሄደው ሰልፍ እስካሁን አደናቃፊ ነው ብለን ያገኘነው ነገር ስለሌለ ከዚህ ጋር ተያይዞ ለህብረተሰቡ የምናስተላልፈው የተለየ የጥንቃቄ መልዕክት የለንም ብለዋል። ሽምብጥ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ ከአንድ አመት በላይ የቆየች አንዲት የአእምሮ ህመምተኛ መሰል  ሴት ሞባይል ስታነጋግር አይተናል በሚል ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ፖሊስ ከትላንት በፊት በቁጥጥር ስር አውሏታል። የያዘችው ሞባይልም በባለሙያዎች ምርመራ እየተደረገበት መሆኑንም ገልጸው''የሬዲዮ መገናኛና ቦምብ ይዛለች'' እየተባለ በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ከዕውነት የራቀ መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህ ባለፈ ህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ መሰረት ከ10 የሚበልጡ ተጠርጣሪ ግለሰቦች  በቁጥጥር ስር ውለው በተቋቋመው ቡድን ምርመራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል። በማህበራዊ ሚዲያ ትክክለኛ ያልሆነና ዕውነትነቱ ያልተረጋገጠ መረጃ የሚያራግቡ አካላትም ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የድጋፍ ሰልፉ ያለምንም የፀጥታ ችግር ተጀምሮ እንዲጠናቀቅም በከተማዋ የተደራጁ ወጣቶች ከፀጥታ አካሉ ጎን በመሆን አስፈላጊውን ሁሉ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙም ኮማንደር ዋለልኝ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም