ሰላም ከራስ ይጀምራል

276

እንግዳ ወርቅ ባዬ (ኢዜአ)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26/2012 ዓ.ም የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ምሁሯ ናይጄሪያዊቷ የሰብአዊ መብትና የዴሞክራሲ አቀንቃኝ ዶክተር ሃፍሰት አቢዮላ እንደምትለው "የሰላም ቁልፉ የሚገኘው በእያንዳንዳችን እጅ ላይ ነው። የሰላም ምንጮችም ሆነ አደፍራሾች እያንዳንዳችን ነን፤ የራሳችንንም ሆነ የሌሎችን ሰላም እውን ለማድረግ  ውስጣዊ ሰላም መፍጠር የሁሉም ነገር መነሻ ነው።" ይህን አቋሟንም በተደጋጋሚ አራምዳለች።

የሃፍሰት አባባል በርካቶችን ሊያስማማ እንደሚችል ይገመታል። ሰላም የምንም ነገር መጀመሪያ መሆን እንዳለበትም አከራካሪ አይሆንም። ለሌሎች ሰላም ለመፍጠር ካስፈለገ ለራስ ሰላም ቅድሚያ መስጠት ግድ ይላል። የሰላም መጀመሪያው የራስ ሰላም ነው፤ ቀጥሎ የሌሎች ሰላም ሲሆን መጠቅለያው የአገር ሰላም ይሆናል።

የሰላም ዋጋዋ ከምንለው በላይ ነው። ሰርቶ ለመግባት፣ ያቀድነውን ለማሳካት፣ የዘራነውን ለማጨድ፣ ራስንም ሆነ አገርን ለመለወጥ፣ ወልዶ ለመሳም ሌላው ቢቀር ያበሰሉትን ለመብላት እንኳ ያለ ሰላም አይሆንም። የሰላምን ጎደሎ የምናውቀውና የምንረዳው ግን እዚህም እዚያም ወጥቶ ለመግባት ፈታኝ ጊዜ ሲገጥመን ነው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ የሰላም እጦቶችን ማስታወስ ይቻላል። አንዱ በሌላው ላይ ጣቱን ሲቀስርና እጁን ሲሰነዝር፣ ወንድም በወንድሙ ላይ የጥፋት ጅራፉን ሲያጮህ፣ በተግባርም ጭካኔ የተሞላባቸው የእርስ በርስ መጠፋፋት ሲፈፀሙ አስተውለናል።

አሁን አሁን መገዳደልና መጠፋፋት፣ አንዱ አንዱን መግፋት የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተከስተው በነበሩ ግርግሮችና ግጭቶች የበርካቶች ህይወት ጠፍቷል፤ አካላቸው ጎድሏል፤ ንብረታቸው በጠራራ ፀሐይ ተዘርፎ የተረፈውም ተቃጥሏል። በዚሁ ሳቢያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ቄያቸውን ለቀው ተሰደዋል። በዕድሜ ዘመናቸውን ከኖሩበት፣ ተወልደው ካደጉበትና ወልደው ከከበዱበት አካባቢ ተፈናቅለው አሁን ድረስ መጠለያ ውስጥ የሚኖሩ በርካቶች ናቸው።

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ላለፉት 20 ዓመታት የነበረው መራራቅና በጠላትነት መተያየት ቀርቶ ሰላም በመውረዱ በአገሮቹና በቀጠናውም የፈጠረውን አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ማየት ይቻላል። ሰላም ወርዶ የሁለቱ አገራት ዜጎች ሲገናኙ በደስታ እንባ ተራጭተዋል። በሰላም እጦት ሳቢያ ሳይሞቱ ተለያይተውና ተነፋፍቀው ቆይተው የሰላም አየር ሲነፍስ መገናኘታቸው ለመለያየት "ሞት ብቻ" ምክንያት አለመሆኑን ቁልጭ አደርጎ አሳይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት እየታየ ቢሆንም የዚያኑ ያክል በየእለቱ ፈታኝ ሁኔታዎች እየገጠሙ መሆናቸው እርግጥ ነው።

በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው የጥፋት እንቅስቃሴ ዛሬም ለጥፋት፣ ላለመረጋጋት እና ለሁከት ብለው የሚሰሩ አካላት ለመኖራቸው አመላካች ሆኗል። ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨት አጋጣሚውን ተጠቅመው የራሳቸውን ፖለቲካዊ ዓላማ እውን ለማድረግ እየሰሩ ያሉ ስለመኖራቸውም እርግጥ ነው።

የብሔርና የሃይማኖት ጽንፍ የያዙ አክራሪ ኃይሎች በየአካባቢው ሰላም እንዲደፈርስ ስንቅ እና ትጥቅ አቀባዮች በመሆን ኢትዮጵያ ወደ ለየለት ትርምስ እንድትገባ መስራታቸውን ቀጥለውበታል። እነዚህ ኃይሎች መንግስት ሲጨክንባቸው መብታቸው እንደተነካ፤ ሲታገሳቸው ደግሞ ፍርሃት እየመሰላቸው በእኩይ ተግባራቸው ቀጥለውበታል። በተጀመረው ለውጥ በይቅር ባይነት በደልን በመተው፤ ፍቅርንና አንድነትን እውን በማድረግ በመደመር እሳቤ ወደ ፊት እንሻገር ቢባሉም ከመሻገሪያ ድልድይ ይልቅ መቀበሪያ ጉድጓድ መቆፈሩን ስራችን ብለው የያዙ አሉ።

ኢትዮጵያዊያን የምንታወቀው በአንድነት፣ በመተዛዘንና በመተጋገዝ መኖርን እንጂ ለበቀልና ቁርሾ ጊዜ አናጠፋም ነበር። ኢትዮጵያዊያን ፋሽስት ኢጣሊያን ለማሸነፍ ያሳዩት አንድነት፣ አልበገር ባይነትና ወኔም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው። ከአድዋ ድል የምንማረውም ጥላቻን ሳይሆን አንድነትን፣ ግጭትን ሳይሆን ፍቅርን መሆኑ እርግጥ ነው።

ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊያን በጥቁር ህዝቦች ላይ የተጣለውን ቀንበር በማንሳት ለአፍሪካዊያን የነጻነት ታጋዮች ፈር ቀዳጅ በመሆን ለጸረ ቅኝ አገዛዝ እንቅስቃሴ ሁነኛ ምሳሌ የሆኑት። አንድ እንጨት አይነድም፤ አንድ እጅ አያጨበጭብም እንደሚባለው አንድነትና ፍቅር ከሁሉም በላይ አሸናፊ እንደሚያደርግ የአድዋ ድል አስተምሮናል። በመተሳሰብና ያለንን በማካፈል መኖር እንጂ ልዩነትን መስበክ ለአገርም ለህዝብም አይበጅም። ምክንያቱም አገር ከብሔርም ከምንም በላይ ናትና። በሃይማኖት፣ በብሔር፣ በጎጥና በመሳሰሉት ጎራዎች መከፋፈልን በኢትዮጵያ ታሪክ የአድዋ ድል አድራጊ አባትና እናቶች አላስተማሩንም። በማንነት ተከፋፍሎ እርስ በርስ ከመጠላለፍ ይልቅ ሕብረትና አንድነት መፍጠር የሁላችንም ቤት ለሆነችው ኢትዮጵያም ዋጋው ትልቅ ነው።

ላለፉት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በስፋት ያቆጠቆጠው የዘር ፖለቲካ ልዩነትን በማስፋት እርስ በርስ ጥርጣሬ መፍጠር እንጂ ትርፉ እምብዛም ሆኖ አልታየም። አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ በአደባባይ እየተነገረ ነው። ያጋመስነውን ዓመት የተቀበልነውም ይሄው የህዝብ አንድነትና ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሚያስችሉ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና የመደመር መርህ እንደሆነ ይታወሳል።

ይሁንና የትናንት በደልና ክፋት ሳይበቃቸው ዛሬም ለሌላ ጥፋት የሚጥሩና የሚዘምሩ የጥፋት ኃይሎች እዚህም እዚያም መኖራቸው እርግጥ ነው። ተግባራቸውም ለራስ ጥቅም ከማሰብ እንጂ ለአገርና ለህዝብ ከመቆርቆር አለመሆኑ ለማንም ግልፅ ነው። በመሆኑም አገራዊ ለውጡ በእነዚህ አካላት ወደ ኋላ እንዳይመለስ ነገሮችን በጥንቃቄ፣ በትዕግስትና በአንክሮ ማየት ጊዜው የሚጠይቀው መሆኑን በተለይ ወጣቶች ሊረዱት ይገባል።

አንዳንድ ወጣቶች የሆነ አካል የጥፋት ማስፈፀሚያ መሳሪያ ከመሆንና በስሜት ከመነዳት ወጥተው “ምን እያደረኩ ነው? አገሬ ከኔ ምን ትጠብቃለች?" ብለው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው። አገርን በልማት ጎዳና በማራመድ የሚፈለገውን ብልጽግና ማምጣት ከተፈለገ እርስ በርስ መፋቀር፣ ቂም በቀልን መተውና አንድነትን ማጠናከር አስፈላጊ ነው። በተዛባና በተጋነነ የታሪክ ትርክት እንዲሁም በበደል የቆሸሸን አዕምሮ ማጽዳትም ያስፈልጋል።

በቀደመ ማንነታችን ብዙ የማይገቡ ተግባራት መሰራታቸው ሀቅ ቢሆንም ለነገ መልካም ነገር ሲባል ካለፈው ጥፋት መማር እንጂ መድገም አይገባም። ዛሬ ላይ ሆነን ትናንት የደረሰብንን በደልና መከራ እያስታወስን፣ ለበቀል ከተነሳን በዘመናችን ሌላ ቂምና ጥላቻ አስቀምጦ ከማለፍ በስተቀር አንዳች የሚገኝ ትርፍ የለውም።

ኢትዮጵያ ወደ ምንፈልገው የብልጽግና ጉዞ እንድታመራና ከእዚያም አትራፊ መሆን እንድንችል የበደሉንን ከመበቀል ይልቅ በይቅርታና በፍቅር ማለፍ ይገባል። በጥላቻ አዙሪት ውስጥ ሆነን ከመቃቃር ይልቅ ህብረት ፈጥረን መንቀሳቀስ አስፈላጊ ነው። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንደታየው ወንድም ወንድሙን የሚገልበትና እንደጠላት የሚተያይበት ሁኔታ ላይመለስ ማብቃት አለበት።

በተለይ ወጣቱ በዘርና በሃይማኖት ከሚከፋፍሉትና የታሪክ ንጥቂያ ውስጥ በገቡ አካላት የሚተረክለትን በደፈናው ከመቀበል ይልቅ ትክክለኛ ታሪኩን ለይቶ ማወቅ አለበት።

"የእኔ ነው፣ ድንበሬ ነው፣ የእኔ ብሔር ነው፣ እገሌ መጤ ነው" ከሚሉና ከመሳሰሉት አስተሳሰቦች ወጥተን በመተማመን፣ በአንድነትና በመተሳሰብ የምንኖርባትን አገር መፍጠር ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የአሁኑ ትውልድ አስተዋጽኦ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል።

"አንተ ከየት ወገን ነህ?" ከሚል የብሔርና የሃይማኖት አክራሪነት ወጥተን እንደ አድዋ አርበኞች አገርን ማስቀደም ስንጀምር የተጀመረው የሰላም፣ የአንድነትና የብልጽግና ጉዞ መሰረት ይይዛል። ጉዟችን ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ የሚቻለውም ወደ ራስ ብቻ ከማሰብ፣ ወንድም በወንድሙ ላይ ለጥፋት ከመነሳትና "ይሄ የእኔ መንደር ነው" ከሚል ስንወጣ ነው። አገራዊ ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲሰፍን ሁላችንም የራሳችን አስተዋጽኦ እንዳለን አውቀን መንቀሳቀስ ይኖርብናል።

መንግስት የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ነገሮችን ለቀቅ ሲያደርግ በአግባቡ በመጠቀም ማጎልበት እንጂ ለጥፋት ማዋል አግባብነት አይኖረውም። የአፈና ጊዜ አልፎ የለውጥ ጭላንጭል በታየበት ወቅት ቁጭ ብሎ በመነጋገር ችግሮችን መፍታት ሲገባ "በደቦ ፍርድ" እርምጃ እየወሰዱ ሌላ በደል መፈጸም የህገ ወጥነት ማሳያ እንጂ የዴሞክራሲ መገለጫ አይሆንም። አሁን ላይ የመጣውን ለውጥና አንፃራዊ ነፃነት በአግባቡ ካልተጠቀምንበት መንግስትን ወደ አምባገነንነት ይፋፋል። የታየውን የነጻነት ጭላንጭል እንደ "ሳሙና አረፋ" በቅፅበት ሊያጠፋው ይችላል።

በአገሪቱ የተላያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች ሕይወታቸውን እስከ መስዋዕት ድረስ ዋጋ ከፍለው የታገሉት ፍትህ፣ እኩል ተጠቃሚነት፣ አገራዊ አንድነት እንዲመጣ እንጂ አገር ለመበታተን እንዳልሆነ ልብ ማለትም ያስፈልጋል።

ዜጎች የሚኖራቸውን ማናቸውም ጥያቄና ቅሬታ በማቅረብ የጋራ መፍትሄ ለማምጣት መስራት ካልቻሉ በስሜት በመናጥ እየተንቀሳቀሱ አገርን ወደ ማጥ ከመክተት ያለፈ ፍሬ ያለው የመፍትሄ ሃሳብ አይወልድም። የደቦ ፍርድና መሰማማት የሌለበትም ጩኽት አገር ያፈርሳል እንጂ አይገነባም። ወጣቶች ምክንያታዊ ጠያቂዎች እንጂ ያለ ምክንያት ለጥፋት ለሚቀሰቅሳቸው ሁሉ "አቤት" ብለው መነሳት አይኖርባቸውም። በህግ አግባብ የማይከናወን ሁሉ ሌላ ጥፋት መውለዱ አይቀርምና ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ በአገሪቱ የተረጋገጠው የለውጥ ጉዞ ህዝቡ ለብዙ ዓመታት ያላገኘው፣ ሲናፍቀው የኖረና በርካቶች የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉበትና ለአካል ጉዳት ጭምር የተዳረጉበት በመሆኑ ወደ ኋላ እንዳይቀለበስ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባዋል። መሪዎች ነገ ያልፋሉ፤ መቸም ቢሆን የማያልፈው አገርና ህዝብ ነው። ለውጡ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ከተፈለገ ለውጡን መምራትና ማስቀጠል ያለበት ህዝቡ ነው። በተለይ ወጣቱ የተገኘውን አንፃራዊ ነጻነት፤ እየተቀነቀነ ያለው ኢትዮጵያዊ አንድነትና ሰላም እንዲጠናከር ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት።

በስሜት ተነድቶ በቡድን ጥፋት ከመፈጸም በመቆጠብ ለዘመናት ሲናፈቅ የነበረውን ነጻነት በአግባቡ መጠቀምና ማጎልበት እንደሚችልም ወጣቱ በተግባር ማረጋገጥ አለበት። "ነጻነት አገኘሁ" በሚል ሰበብ ማንም ሰው ቢሆን ከህግ ውጭ መንቀሳቀስ የለበትም። ምክንያቱም ዛሬ በግብታዊነት የምንፈጽመውን ጥፋት ለነገ የአገር ጥፋትና የመፍረስ አደጋ በር ከፋች ነውና። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት እንኳን በጥሩ ታሪክነት የሚወሱና በእኩይ ምግባርነት የሚነቀፉ የተለያዩ ነገሮችን ማስታወስ ይቻላል። ሁላችንም ቢሆን ጥሩውን ጅምር ለማስቀጠል መጥፎውን በማረም በመልካም ተግባር መቀየር እንጂ "ሂሳብ ለማወራረድ" መነሳሳት ሌላ ጥፋት ይወልዳል እጂ አገራዊ ትርፍ የለውም።

ከፍቅርና ከአንድነት እንጂ፤ ከጥላቻና ልዩነት የሚገኝ አንዳችም ትርፍ እንደሌለ የተገነዘቡ አሁንም ለአገራቸው ሌት ተቀን እየታተሩ ነው። ኢትዮጵያዊያን ማጠናከር ያለብንም መልካም ተግባርን እንጂ እኩይ ተግባርን መሆን የለበትም። "ጥፋት ጥፋትን ይወልዳል፣ እልህ መጥፎ ነው ይጎዳል" የሚለው የሁላችንም መርህ መሆን አለበት። ለአገር መሞት ክብር ነው ብለው ጀግኖች አርበኞች በየዱር ገደሉ ህይወታቸውን ሰውተው ነጻነት ሸልመውናል። ስልጣኔ በሌለበት በእዚያ ዘመን እንኳ የሰውና የአገር ክብር የገባቸው ጀግኖች አርበኞች ልዩነታቸውን ወደ ጎን ብለው አንድነትን ነው የመረጡት። ያ ተግባራቸው ዛሬ ላይ ፍሬ አፍርቶ ኢትዮጵያን ከእነ ካባዋ አኑሮልናል።

የሚሻለውና የሚጠቅመው ያለንን ማካፈል፣ ለሌላውም መኖርና ወገናዊነትን ማሳየት ነው። ሕብረትን ማጠናከር የአንድ ሰሞን ሥራ ሳይሆን ሁሌም ልናከናውነው የሚገባ ተግባር መሆን አለበት። እኛ ዛሬ የምንኖርባት ኢትዮጵያ በነጻነት የቆየችው ከወራሪ ጠላት ለመከላከል ጀግኖች አባቶችና እናቶች ደምና አጥንታቸውን በመገበራቸው ነው። የዘመኑ ዋነኛ ጠላታችን የሆነውን ድህነት ደግሞ አንድነታችንን በማጠንከርና ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ድል ማድረግ ይኖርብናል። ድህነትን ከትውልድ ትውልድ መቀባበልን ዛሬ ላይ በቃህ ልንለው ይገባል። እንደ አባቶቻችን ጦር፣ ጋሻና ጎራዴ መምዘዝ ካለብን ለድህነት እንጂ ለሌላ ጠላት አይደለም። ይህ ሲሆን ልማትና ብልጽግና ይረጋገጣል፤ ሰላም ይሰፍናል። ደግሞም ዛሬ የሰራነው አኩሪ ታሪክ የነገ ህያው ምስክር ይሆናል።

ለመኖር መስራት አስፈላጊ የመሆኑን ያህል ሰርቶ ለመለወጥና አገርን ወደ ብልጽግና ጎዳና ለመምራት ሰላም ወሳኝ ነው። በመሆኑም ሁሌም ለሰላም ትኩረት መስጠት አለብን። ለእዚህ ደግሞ የቀደመ በደልን ትቶ በፍቅር፣ በአንድነትና በመተሳሰብ መጓዝ ግድ ይላል።

የቂምና የበደል ዕዳን ይዘን የምንጓዝ ከሆነ ነገ ታሪክ የሚያስታውሰን በበጎ ሳይሆን በጥፋት የታሪክ ፋይል ይሆናል። ሁሌም የሰላም አርበኞች እንጂ የግጭትና ጥላቻ አቀንቃኞች መሆን የለብንም። ዶክተር ሃፍሰት አቢዮላ እንዳለችውም ሰላም ከራስ የውስጥ ስሜት ይጀምራል። ውስጣችን ሰላም ካልሆነ ራሳችንን ረብሸን ለቤተሰባችን የሚተርፍ እንከን እንፈጥራለን። የቤተሰብ ሰላም እጦት ወደ ጎረቤት መጋባቱ አይቀርምና እዳው ለሌላም ይተርፋል። የራስ ውስጣዊ ሰላም የአገር ሰላም መነሻ ነውና ሁላችንም ለሰላማችን እንትጋ፤ ሰላማችን ይብዛ!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም