አገር በቀል ጥንስስ

146

አሰለሞን ተሰራ /ኢዜአ/

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር ወደ ኃላፊነት እንደመጣ ከወጠናቸው ዋነኛ ስራዎች መካከል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱ ሲሆን የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ ማዞር ደግሞ ቅድሚያ ተሰጥቶታል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ዓመታት በሁለት አሀዝ ማደጉ፣ የነፍስ-ወከፍ ገቢ በከፍተኛ መጠን መጨመሩ፣ የድህነት ምጣኔ መቀነሱ፣ ምርታማነት መጎልበቱ፣ በጤናና ትምህርት ዘርፎች ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡ እንዲሁም በመሠረተ ልማት ግንባታ ትልቅ እመርታ መታየቱ በኢኮኖሚ ማሻሻያው የቀደሙ ስኬቶች ዝርዝር ውስጥ ተካቷል።

የስኬቶቹ ምንጭ የመንግስት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ፈሰስ መሆኑ ታይቷል። ከፋይናንስ ምንጮቹ መካከልም ቁጠባ ተጠቅሷል፤ የቁጠባ መጠን ከ10 በመቶ ወደ 24 በመቶ ገደማ መድረሱ በመንግስት ከተተገበሩ የቤቶች ቁጠባ፣ የጡረታ አበል ቁጠባና የመሳሰሉ ምክንያቶች ጋር ተያይዟል። 

አገሪቷ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ጎራ ለመቀላቀልና ዝቅተኛውን መሥፈርት ለማሟላት የነፍስ-ወከፍ ገቢን በሶስት እጥፍ ማሳደግ፣ የድህነት ምጣኔን በግማሽ መቀነስና መሠረተ ልማት ማስፋፋት ላይ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ አለባት። ለምሳሌ በውሃና በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከ40-45 ሚሊዮን ተጨማሪ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቃል። 

ሆኖም ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት መንግስት በበላይነት የያዛቸውን የልማት ድርጅቶቹን ለምን ለመሸጥ ፈለገ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። በተለይም የፕራይቬታይዜሽኑ አካሄድ እንደ ዓለም ባንክ ባሉ ተቋማት የቀረበ የርዕዮተ ዓለም ተፅዕኖ ውጤት ነው ሲሉ የሚቃወሙ የዘርፉ ተንታኞች አልጠፉም።

ነገር ግን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ማዕቀፉ ሶስት ምሰሶዎች አሉት፤ እነዚህ ምሰሶዎች የማክሮ-ኢኮኖሚ፣ የመዋቅራዊ ወይም ተቋማዊ እና ሴክተር ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ በሶስቱ ክፍሎች የተመለከቱትን ማነቆዎች ኢላማ ያደረጉ ናቸው። 

ዋነኞቹ ግቦችም የስራ ዕድል መፍጠር፣ ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ፣ ድህነትን መቀነስና ኢኮኖሚውን በማበርታት አገሪቷን ወደ ብልጽግና ማሸጋገር ነው።

የማክሮ-ኢኮኖሚ ሚዛን አለመስተካከል ባለሃብቱ፣ የንግዱ ማህበረሰብና ሸማቹ በኢኮኖሚው ላይ እምነት እንዳይኖረው ያደርጋል። ይህንን ለመለወጥ ማሻሻያው /ሪፎርም/ የውጭ ምንዛሬ፣ ፋይናንሺያል ሴክተር፣ ፐብሊክ ሴክተር እንዲሁም ሞኒተሪ እና ፊስካል ሴክተሮችን ይነካል።

እነዚህ ማሻሻያዎች እርስ በእርሳቸው ተደጋጋፊና የኢኮኖሚውን እድገት ዘላቂነት ባለው መልኩ የሚደግፉ ሲሆኑ የዕዳ ጫናውን በመቀነስ በኩል ሚናቸው ትልቅ ይሆናል።

ከዚህ በመነሳት የመንግስት የልማት ስትራቴጂ ማሻሻያዎች የግሉን ዘርፍ በማሳደግ፣ ተወዳዳሪነትን በማጎልበት ወደ አገሪቷ የሚገባውን ኢንቨስትመንት እንደሚያሳድጉ ታምኖበታል። ይህም ለዘመናት የዘለቀውን የመንግስት የኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነት ያስቀረዋል ተብሎ ይገመታል።

በቅርቡ የፀደቀው አዲሱ የኢንቨስትመንት አዋጅ አገሪቷ በጀመረችው የለውጥ ጉዞ ላይ ቅመም በመሆን ያገለግላል። እ.አ.አ በ2012 የወጣውን የኢንቨስትመንት አዋጅ የተካው አዲስ ህግ የተወሰኑ ዘርፎችን ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ ቢያደርግም በርካቶችን ለውጭ ባለሃብቶች ሙሉ በሙሉና በከፊል ክፍት አድርጓል።

ይህንኑ ተግባር መቀመጫውን ለንደን ያደረገውና የዓለም ባንክ አካል የሆነው ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን እ.አ.አ ማርች 2019 ”የአገሪቷ የግል ዘርፍ ማከሚያ" በማለት ባሳተመው ጽሑፍ ላይ ጠቅሶታል።

"አሁንም በመንግስት ተጽእኖ ስር የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች አሉ። የፋይናንስ ዘርፉ፣ ቴሌኮም፣ ሎጀስቲክ እና ትራንስፖርት ይጠቀሳሉ። በቴሌኮምና በሎጀስቲክ ዘርፍ ለግሉ ዘርፍ ክፍት የተደረገው ማሻሻያ ተወዳዳሪነትን በእጅጉ ያጎለብታል። የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የምንዛሬ ተመን አስቸኳይ መፍትሄ የሚፈልጉ ጉዳዮች ናቸው፤ ያም ቢሆን ነገሮች በጥሩ ሁኔታ እየተጓዙ መሆኑን ተመልክተናል" በማለት የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ተጠሪ ቼኪ ዑመር ሲላ ተናግረዋል።

በአገሪቷ ያለው የድህነት ምጣኔ 26 በመቶ ቢጠጋም ኢንቬስተሮችን ለመሳብ የሚያስችሉ በርካታ እድሎች እንዳሏትም ይታወቃል። በየዓመቱ በ10 በመቶ የሚያድገው ኢኮኖሚ እ.አ.አ በ2020 በሰባት በመቶ እንደሚያድግ ዓለም ባንክ ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።

ኢትዮጵያ በቀጠናው ካለው 5 ነጥብ 4 በመቶ አማካይ የኢኮኖሚ እድገት ከፍ ያለውን ምጣኔ በማስመዝገብ በዓለም በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ አገራት አንዷ ሆናለች። በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ ስትሆን 70 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧም ከ30 ዓመት በታች የሚገኝ ወጣት ነው። ይህም መስራት የሚችልና ሰፊ የገበያ አቅም ያለው መሆኑ ይታወቃል በማለት ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ያወጣው ሐተታ ያሳያል።

በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉና በኢትዮጵያ የከተሙ የንግድ ተዋናዮች አዲሱን የኢንቨስትመንት ህግ በአዎንታዊ ጎኑ ተቀብለውታል። በተለይም ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት የተደረጉት ዘርፎችና ማሻሻያዎች ተነሳሽነታቸውን እንደጨመረው ይናገራሉ።

የአሜሪካ ንግድ ምክር ቤት የኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ርብቃ አርአያ የተደረገው ማሻሻያ በርካታ የውጭ ካፒታልና ባለሙያዎችን እንደሚስብ ታምናለች። "ከዚህ በፊት የነበረው ክልከላ መነሳቱ ኢንቬስተሮችን ለመሳብ ያስችላል፤ በቅርቡ በጋራ መስራት የሚፈልጉ ግዙፍ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ተቋማትን ማየት እንችላለን" በማለት ተስፋዋን ገልጻለች።

ከዚህ ባለፈ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው የኢንቨስትመንት ቦርድ ከግሉ ዘርፍ ሁለት ተወካዮች መካተታቸው አዎንታዊ ለውጥ መሆኑንም አክላለች።

መንግስት የአገሪቷን የቴሌኮም ዘርፍ 49 በመቶ ድርሻ ለባለሃብቱ ክፍት ማድረጉ የዚሁ አካል ሲሆን ሁለት የውጭ የግል ተቋማት በዘርፉ እንዲሰማሩ ፈቃድ የመስጠት እቅድ መያዙ ለዚህ ማሳያ ነው። በዘርፉ የሚደረገው ማሻሻያ ተወዳዳሪነቱን በማጎልበት የተሻለ አገልግሎት፣ ዝቅተኛ ዋጋና አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን የሚያስፈልገውን የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ካፒታልና ባለሙያ ለማግኘት ያስችላል።

"ወደ ቴሌኮሙ ዘርፍ ለመግባት የተገኘው ዕድል በአፍሪካ በሕዝብ ብዛቷ ሁለተኛ በሆነችው አገር ለመስትራ ትልቅ አጋጣሚ ነው" በማለት በኢትዮጵያ በሚከናወኑ በርካታ ዘርፎች ላይ ኢንቨስት በማድረግ የተሰማራው የእንግሊዝ የልማት ፋይናንስ ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ ቪቪያን ኢንፋንቴ ተናግረዋል።

አዲሱ ደንብ ገደቦችን በመቀነስ አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንና በህብረተሰቡ አኗኗር ላይ መልካም የሚባል ተፅእኖ ለመፍጠር እንደሚያስችልም ጠቁመዋል። የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም እ.አ.አ በ2019 ባወጣው ዓለም አቀፍ የተወዳዳሪነት መስፈርት የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ እድገት ከ140 አገራት 107ኛ ላይ አስቀምጦታል።

በአገሪቷ ያሉ የግሉ ዘርፍ ባለሃብቶች ከባንኮች የሚያገኙት ብድር 16 በመቶ ብቻ ሲሆን በኬንያ 51 በመቶ፤ ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ደግሞ 41 በመቶ መሆኑን በማነጻጸር ብዙ መስራት እንደሚጠበቅም ምክረ ሃሳቡን አስቀምጧል።

በአገሪቷ ንግድ ለማከናወን ያለው መልካም እድል ብድር ከማግኘት አንጻር ሲሰላ ከዓለም 190 አገራት 176ኛ ላይ መቀመጡ ዘርፉ መሻሻል እንዳለበት ጠቋሚ ነው።

እ.አ.አ በ2019 የወጣ የፋይናስ ሪፖርት እንደሚያሳየው የባንክ ተደራሽነቱ ፆታዊ ስብጥር ክፍተት ያለበት ሲሆን 29 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የባንክ ተቀማጭ ሲኖራቸው 41 በመቶ ወንዶች ተመሳሳይ ተቀማጭ አድርገዋል። ለወጣቶች ብድር የሚያቀርቡ ተቋማት በአግባቡ ባለመደራጀታቸው ብድር የሚያገኙ ጎልማሶች ከአምስት በመቶ እንደማይበልጡም ተጠቅሷል። የሰው ሃብት ልማቱም ዝቅተኛ በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሄ ይፈልጋል።

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያደረገች ያለው እንቀስቃሴ ዘላቂ የገበያ እድል በማስገኘት የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ወደፊት እንደሚያራምደው ታምኖበታል። ተግባሩ የመንግስትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ሲሆን ግልጽና ተገማች የንግድ መዋቅር በመዘርጋት የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቬስተሮችን ለመሳብ ያግዛል በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋና የኢኮኖሚ አማካሪ ማሞ ምህረቱ የዓለም ንግድ ድርጅት ለሚያሳትመው መጽሔት በትዊተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ የኒውዮርክ ኮንቬንሽኖች አባል መሆኗ ዓለም አቀፍ የንግድ አለመግባባቶች በዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ፍርድ ቤቶች እንዲዳኙ ያስችላል፤ ይህም ለኢንቬስተሮች ተጨማሪ መልካም እድል ተደርጎ ይቆጠራል በማለት ርብቃ አርአያ ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም የበኩሉን መሰረታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ሲሆን እድገትን ታሳቢ ያደረጉ ዘርፎቸን በመለየት ለኢንቬስተሮች እያስተዋወቀ ነው። የኢንቨስትመንት ጥያቄ የሚቀበልበትን አሰራር ቀልጣፋ ለማድረግ የኦንላይን ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ተግባራዊ አድርጓል።

ለተለየ አገልግሎት ተብለው የተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ለኢንቬስተሮች አዲስ አማራጭ መሆናቸውንና ዘርፎቹ በቂ የሰው ኃይል በአነስተኛ ዋጋ ለማግኘት እንደሚችሉ ኮሚሽነሩ አበበ አበባየሁ መናገራቸውን ዘገባው አስነብቧል።

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዓለም አቀፍ ድጋፍ እያገኘ የመጣ ሲሆን የዓለም ባንክ የደረቅ ወደብ አገልግሎት መዳረሻ ለመገንባት የሚያግዝ 150 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ሲያደርግ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ በበኩሉ አገር በቀሉን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመደገፍ 3 ቢሊዮን ዶላር ብድር ሰጥቷል።

ብዙ ተመልካቾች እንደሚስማሙበት መንግስት የጀመረው የኢኮኖሚ ማሻሻያ በርካታ የግል ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያግዛል።

መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የኢንቨስትመንት ተቋም የፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ሊቀመንበር ዘመዴነህ ንጋቱ በኢትዮጵያ መጻኢ እድል ብሩህ ተስፋ እንደሚታያቸው ይናገራሉ።

"ዘወትር በማደግ ላይ ያለ ገበያን እንመለከታለን፤ ኢትዮጵያም በአፍሪካ ዋናውንና ከፍተኛውን እድል ይዛ ብቅ ብላለች። መንግስትም የያዘውን ሚና ለመቀነስ የወሰደው እርምጃ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ያለውን ሚዛን በማመጣጠን የኢንቬስተሩን በራስ መተማመን ያሳድጋል። ማሻሻያው በመንግስት የበላይ ሃላፊዎች ቁርጠኝነት የተደገፈ መሆኑ ስኬታማ እንደሚያደርገን እንድንተማመን አድርጎናል" ነው ያሉት።

ለዚህ ይረዳ ዘንድ በጥንቃቄ የተዘጋጀ ፊስካል ፖሊሲ መከተል ወሳኝ ነው። የውጭ ምንዛሬ ገበያውን በተመለከተ የአጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሄዎች ተቀምጠዋል። ተቋማትን ወደ ግል ይዞታ ማዘዋወር፣ የዕዳ ጫናን የማያስከትሉ የውጪ ብድርና ከውጭ አገር በሀዋላ የሚላኩ ምንዛሬዎችን የማበረታቻ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ከአጭር ጊዜ መፍትሄዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

የውጭ ምንዛሬ አቅም በዚህ መልኩ ሲሻሻል በሂደት ወደ ምንዛሬ ገበያ አሠራር ማሻሻያ መሄድ ይቻላል። የፋይናንስ አቅርቦትን ለማሻሻል የፋይናንሺያል ሴክተር እና የካፒታል ገበያ መፈጠርና መጎልበት ለስኬቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይረዳል።

ሴክተርን በተመለከተ በተለየ መልኩ መፍትሄ የሚፈልጉ ጉዳዮች ተለይተዋል። በተለይ የግብርና ግብዓት አቅርቦትንና ውጤታማነቱን ከማሻሻል ጀምሮ እንደ መስኖ ያሉ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ማስተካከል፣ የመሬት አጠቃቀም እንዲሁም የግብርና ልዩ ፋይናንስና ኢንሹራንስ ማዘጋጀት ታሳቢ መደረጋቸው በኢኮኖሚ ማሻሻያው ላይ ተቀምጧል። 

በማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ሌሎችም ዘርፎች ማነቆዎች ተለይተው የመፍትሄ አቅጣጫዎች መዘጋጀታቸው ለኢኮኖሚ ማሻሻያው ስኬት አስቻይ መደላድሎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም