“ግድቡ የኛ የኢትዮጵያዊያን ነዉ”!

57

ገዛሄኝ ደገፉ (ከኢዜአ)

በአሜሪካ  እና በዓለም ባንክ ታዛቢነት በህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቅ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ ሲያካሂዱት የነበረው ድርድር ፌብሩዋሪ 27 እና 28 ይፈረማል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ በስብሰባው ላይ እንደማትገኝ ማሳወቋን ተከትሎ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር “ኢትዮጵያ ስለ ህዳሴው ግድብ ስምምነት ላይ ሳይደረስ የውኃ ሙሌትም ይሁን ሙከራ እንዳታደርግ” የሚል ማሳሰቢያ አዘል መግለጫ አውጥቷል።

ግብጽ በበኩሏ ወሳኝ የሚባለውን ሥምምነት ሳይደረስ ታላቁ የህዳሴ ግድብን በያዝነው ዓመት ውኃ ለመሙላት መወሰኗ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጣረስ፤ ሶስቱ ሃገራት ከአምስት አመታት በፊት የተፈራረሙትን ስምምነት የሚያበላሽ መሆኑን በመግለጽ በኢትዮጵያ የሚደረጉ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ለመመከት ዝግጁ መሆኗን ይፋ አድርጋለች። የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የውኃና መስኖ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በተከታታይ ሲያወጧቸው የነበሩ መግለጫዎች ይህንኑ የሚያጠናክሩ ናቸው።

ኢትዮጵያ በዋሽንግተን ስብሰባ ላይ እንደማትገኝ ካሳወቀች በኋላ የግብጽ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ ምሁራኖቻቸውን በማነጋገር ሰፋ ያለ ዘገባ በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ምሁራን ከሚያነሷቸው ጉዳዮች መካከል በዋናነት “ኢትዮጵያ በድርድሩ ያልተገኘችው ከፊት ለፊት ምርጫ ስላለ ተቃውሞ እንዳይገጥማት ሂደቱ እንዲራዘምና ጊዜ ለመግዛት ነው፣ ጉዳዩ ወደ ተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት መወሰድ አለበት፣ ስምምነት ሳይደረስ ውሃ መሞላት የለበትም” የሚሉት ይገኙበታል።

ኢትዮጵያ በአሜሪካ የቀረበው ሰነድ የሶስቱ ሀገራት የድርድርም ሆነ የሕግ እና ቴክኒክ ቡድኖች ውይይት ውጤት ካለመሆኑም በተጨማሪ የቴክኒክ ጉዳዮችና የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቱ ላይ በሶስቱ አገራት የሚደረገው ድርድር ያልተጠናቀቀ መሆኑን በመጥቀስ “በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም እና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርሆዎች” መሰረት የግድቡ ግንባታና የውኃ ሙሌት ስራዎችም ጎን ለጎን እንደሚቀጥሉ  አቋማን በአጽንኦት አሳውቃለች።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ትልቅ ዋጋ የከፈለበት እና እየከፈለበት የሚገኝ ሀገራዊ ምልክት የሆነው ፕሮጀክት በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ የጋራ መግባባት የፈጠረ ነው። ለዚህም ነው በሰሞኑ የአሜሪካ መንግስት ለግብጽ የወገነ መግለጫ ላይ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ባሉ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ቁጣ የቀሰቀሰ ሆኖ የሰነበተው።

ይህ የአሜሪካ መንግስት መግለጫ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን የውጭ አገራት መሪዎችና ታዋቂ ግለሰቦችም ጭምር ተቃውመውታል። በኢትዮጵያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሺን በይፋዊ ብሎጋቸው ላይ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ግብጽ ስምምነቱ ላይ ያሳየችውን ቁርጠኝነት በማድነቅ፤ ለኢትዮጵያ ደግሞ ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ ማውጣቱ “ግርታ የሚፈጥርና የሚያስገርም ነው” ሲሉ አስፍረዋል፡፡ አያይዘውም አሜሪካ ለግብጽ መወገኗን የሚያሳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል አሜሪካዊው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ጄሲ ጃክሰን ጉዳዩን በማስመልከት ባሰፈሩት ሰፊ ትንታኔ “ግብጽ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቅኝ ገዥ የመሆን ግልጽ ፍላጎት እንዳላት ያመለክታል” ሲሉ ጠንከር ባለ ትችት መግለጻቸውን  አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ አስነብቧል።። አያይዘውም ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨትና ህዝቧን ከድህነት ለማላቀቅ መሆኑን በመጥቀስ ግብጽ በኮሎኒያል ዘመን በናይል ወንዝ ላይ የነበራትን የበላይነት ለማስቀጠል ህግን የጣሰ ፍላጎት እያሳየች ነው ሲሉ ኮንነውታል።

በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር አብደል ቢላል አብደልሰላም ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሱዳን ለግብጽ እንደወገነች ተደርጎ እየተስተጋባ ያለው ነገር ከእውነት የራቀ መሆኑን ጠቅሰው  ሱዳን ታላቁ ህዳሴ ግድብን መደገፏንና በጋራ መስራቷን ትቀጥላለች ሲሉ ተናግረዋል። አያይዘውም ሱዳን ባላት እውነተኛ ፍላጎት ለግድቡ ያልተቆጠበ ድጋፍ ስታደርግና ከኢትዮጵ ጋር በትብብር ስትሰራ መቆየቷን አመልክተዋል።

በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን “ግድቡ የእኛ የኢትዮጵያውያን ነው” ሲሉ ያላቸውን አቋም በተለያዩ የሚዲያ አውትሌቶች እያስተጋቡትና መላው ኢትዮጵያውያንም እየተጋሩት ይገኛል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)የሀገር ጥቅም እና ሉዓላዊነት ላይ ባለመደራደር ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት እንዲቆሙ ጥሪውን አስተላልፏል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አባልና አክቲቪስት ጃዋር ሞሃመድ በማህበራዊ ድረ ገጻቸው  ባሰፈሩት ጽሑፍ "አሜሪካ በምትሰጠው እርዳታ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር መሞከሯ ትልቅ ስህተት ነው" በማለት “አሁን ኢትዮጵያ የወሰደችው አቋም ትክክል በመሆኑ ሁላችንም እንደግፋለን” ነው ያሉት። በሌላ በኩል አንጋፋው የውሃ ፖለቲካ ምሁርና ተንታኝ አቶ ፈቂ አህመድ ነጋሽ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ወንዝ፣ በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት እየተገነባ ያለና ከኢትዮጵያ የውሃ ድርሻ የሚሞላ በመሆኑ ግድቡን የመሙላትም ሆነ ያለመሙላት ውሳኔ የኢትዮጵያ መንግስት እንጂ የሌሎች አካላት ሊሆን አይችሉም ሲሉ ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ወንዝ፣ በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት እየተገነባ ያለና ከኢትዮጵያ የውሃ ድርሻ የሚሞላ በመሆኑ ግድቡን የመሙላትም ሆነ ያለመሙላት ውሳኔ የኢትዮጵያ መንግስት እንጂ የሌሎች አካላት ሊሆን አይችልም የሚለው አቋም የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ አቋም ሆኗል።

መላው የኢትዮጵያ ልጆች “ግድቡ የእኛ የኢትዮጵያውያን ነው” የሚለውን መሪ መልእክት በማንገብ የተጀመረውን ስራ ለማፋጠን ቆርጠዋል። መንግስትም የመሪነት ሚናውን እየተወጣ ይገኛል። ለዚህም ተቋርጦ የነበረውን የ8100A የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሃግብርን ጨምሮ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ተነድፈው በይፋ እየተጀመሩ ነው።

አዎን ግድቡ የእኛ የኢትዮጵያውያን ነው!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም